በሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በሱዳን ጦር መካከል የተጀመረው ጦርነት ከ31 ወራት በላይ አስቆጥሯል
በሱዳን 14 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታቸው መፈናቀላቸውን አይኦኤም ገለጸ።
አለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት(አይኦኤም) ኃላፊ በትናንትናው እለት እንዳስታወቁት ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዳናውያ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
ከቤታቸው የተፈናቀሉት ሱዳናውያን በሀገር ውስጥ ወይም የሀገሪቱን ድንበር አቋርጠው ተሰደዋል ያሉት የድርጁቱ ኃላፊ ከባለፈው ወር ወዲህ 200ሺ ሰዎች መሰደዳቸውን ገልጸዋል።
"11 ሚሊዮን ህዝብ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሲሆኑ 3.1 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ድንበር አቋርጠው ተሰደዋል። በእርግጥ ቁጥሩ ከ14 ሚሊዮን በላይ ነው"ሲሉ የአይኦኤም ዋና ዳይሬክተር አሚ ፖፔ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ ቆየት ብለው እንደገለጹት የተፈናቃዮቹ ቁጥር በሱዳን የእርስበእርስ ግጭት ከመጀመሩ ከሚያዝያ 2023 በፊት የተፈናቀሉትንም ያካትታል።
በሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በሱዳን ጦር መካከል የተጀመረው ጦርነት ከ31 ወራት በላይ አስቆጥሯል።
የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ በሽግግሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ለተወሰነ ጊዜ ስልጣን ተጋርተው ነበር።
ነገርግን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ከሱዳን ጦር ጋር መቀላቀል አለበት በሚለው ጉዳይ አለመግባባቶች በፈጠራቸው፣ ሁለቱ ጀነራሎች ጦራቸውን አስልፈው ወደውጊያ ገብተዋል።
አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ በተለያየ ጊዜ ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።