ተማሪዎች ቢያንስ ሶስት ቋንቋዎችን እንዲማሩ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ
ረቂቅ አዋጁ በወሲብ ጥቃት ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች በመምህርነት እንዳይቀጠሩ አልያም ትምህርት ቤት እንዳይከፍቱም ይከለክላል
እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ያሉ ተማሪዎችን በደረጃ ማስቀመጥንም ረቂቅ አዋጁ ይከለክላል
ተማሪዎች ቢያንስ ሶስት ቋንቋዎችን እንዲማሩ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡
ኢትዮጵያ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅን ለማሻሻል ያለመ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅታለች፡፡ ይህ ረቂ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ በትናንትናው ዕለት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም ይህን ረቂቅ አዋጅ ተጨማሪ ውይይቶች እና ሌሎች ግብዓቶች እንዲታከሉበት በሚል ለዝርዝር እይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
አል ዐይን የተመለከተው ይህ ረቂቅ አዋጅ እንደሚለው ከሆነ ተማሪዎች ስለ ሚማሯቸው ቋንቋዎች፣ ስርዓት ትምህርት ዝግጅት፣ መምህራን ቅጥር፣ ተማሪዎች ምዘና፣ ትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ መንገዶች እና ሌሎችንም ጉዳዮች ይዟል፡፡
ቋንቋዎችን አስመልክቶ በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደተቀመጠው የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንደ ትምህርት አይነትነት እና እንደ ማስተማሪያ ቋንቋነት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ የሚሰጥ ሆኖ እንደ ትምህርት አይነትነት እና እንደ ማስተማሪያ ቋንቋነት መሰጠቱ የሚያበቃበትን የክፍል ደረጃ ክልሎች ይወስናሉ ብሏል፡፡
እንዲሁም የእንግሊዘኛ ቋንቋን በማስተማሪያነት በግዴታ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ማስተማር ግዴታ ነው የተባለ ሲሆን ክልሎች ግን ከዚያ በፊትም የማስተማሪያ ቋንቋ ማድረግ ከፈለጉ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ተማሪዎች ቢያንስ ሶስት ቋንቋዎችን እንዲማሩ ይደረጋል የተባለ ሲሆን የአፈጻጸም መመሪያ በቀጣይ እንደሚወጣም ረቂቅ አዋጁ ያትታል፡፡
እንዲሁም አንድ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ከፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋዎች መካከል የተማሪን አልያም የወላጅን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ ከ3ኛ-10ኛ ክፍል ድረስ እንዲማሩ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ አንድ ተጨማሪ የውጭ ቋንቋ ክልሎች በሚመርጡት መሰረት ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በአማራጭነት ይሰጣል የተባለ ሲሆን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ደግሞ ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡
የተማሪዎች ምዘናን በሚመለከት ደግሞ እስከ 1ኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ የሚባለው እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ተማሪዎችን በደረጃ ማስቀመጥን ይከለክላል፡፡
ከክፍል ወደ ክፍል መዘዋወርን በሚመለከት ደግሞ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ከክፍል ወደ ክፍል ማለፍ የሚቻለው ተማሪዎች በሁሉም ትምህርት አይነቶች 50 ከመቶ እና ከዛ በላይ ውጤት ሲያመጡ ብቻ ነውም ተብሏል፡፡
ክልላዊ ፈተናዎችን ማለፍ ያልቻሉ ተፈታኞች ከሁለት ጊዜ በላይ በነጻ ፈተና ላይ መቀመጥ አይችሉም የተባለ ሲሆን ተፈታኞች በግላቸው እንዲፈተኑ ይደረጋል ይላል ረቂቅ አዋጁ፡፡
በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይም የመምህራንን ትምህርት እና ስልጠና ጉዳዮችን በሚዘረዝርበት አንቀጽ ስር ሴቶች ለመምህርነት ስልጠና በሚወዳደሩበት ጊዜ ለምልመላ የሚያስፈልጉትን አጥጋቢ መስፈርት አሟልተው በውድድር ወቅት ከወንዶች ጋር እኩል ነጥብ በሚያገኙበት ወቅት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ደንግጓል፡፡
እንዲሁም አንድ መምህር በስራ ላይ እያለ በመንግስት ወጪ ደረጃውን የሚሻሽል ስልጠና ከወሰደ ለእያንዳንዱ የስልጠና ዓመት አንድ ዓመት በሙያው ማገልግል አለበት ሲልም ግዴታ ተጥሏል፡፡
ሚዲያን የማገድ ስልጣን ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ቦርድ እንዲነሳ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ
ከዚህ በተጨማሪም ወሲባዊ ጥቃትን የሚመለከቱ ወንጀሎች መፈጸሙ ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆኑ የተረጋገጠበት ሰው በማንኛውም የትምህርት ተቋም ውስጥ በመምህርነት እንዳይቀጠር አግዷል፡፡
አንድ መምህር የሙያ ፈቃዱን በየሁለት ዓመቱ ከክፍያ ነጻ በሆነ መንገድ ማሳደስ እንዳለበት የደነገገ ሲሆን የስራ ፈቃድ ለማግኘት ከምረቃ በኋላ የ2 ዓመት ልዩ የመምራን ሙያ ስልጠናን መውሰድ እንዳለበትም በረቂ አዋጁ ለይ ተደንግጓል፡፡
የግል ትምህርት ቤትን ማቋቋም ስለ ሚከለከልበት ሁኔታ በሚያትተው አንቀጽ ስር በፍርድ ቤት የመክሰር ውሳኔ የተሰጠበት ወይም እዳ መክፈል ያልቻለ ሰው፣ ትምህርት ቤቱን ለማቋቋም ፈቃድ ከሚጠይቀው አመልካች ውስጥ ድርሻ ያለው ሰው በወሲባዊ ወንጀል አልያም በህጻናት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ጥፋተኛ መሆናቸው በፍርድ ቤት የተወሰበት ሰው ፈቃድ ማግኘት አይችልም ብሏል፡፡
በመጨረሻም መንግስት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ትምህርትን በብቃት እና በጥራት ለማዳረስ ያለበትን ግዴታ ለመወጣት ሀገር አቀፍ የትምህርት ፈንድ እንዲቋቋም አዋጁ ይፈቅዳል ይላል፡፡