የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ተከበረ
የኢሬቻ በዓል በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ለ4ኛ ጊዜ ተከብሯል
የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የእርቅና የይቅርታ በዓል እንደሆነ ይገለጻል
የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት አካል እንደሆነ የሚገለጸው እና የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪን የሚያመሰግንበት የ'ሆራ ፊንፊኔ' የኢሬቻ በዓል በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በአዲስ አበባ የሚከበረው የእሬቻ በዓል ሆራ ፊንፊኔ ሲሰኝ በነገው እለት በቢሸፍቱ የሚከበረው ደግሞ ሆራ አርሰዲ ነው።
ሆራ ፊንፊኔን በአዲስ አበበ ለማክበርብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ በዓሉ በሚከበርበት በስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው የእሬቻ ፖርክ ተገኝቷል።
የበዓሉ ስነ ስርዓት የተጀመረው በገዳ ሥርዓት መሰረት በአባ ገዳዎች ምርቃት ነው።
በበዓሉ ላይ ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ሆራ ፊንፊኔ በማቅናት በባህሉ መሰረት ለፈጣሪያቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ወደ መጡበት ተመልሰዋል።
ከአዲስ አበባ እና ከዙሪያዋ እንዲሁም ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ለበዓሉ በባህል አልባሳት ደምቀው በሆራ ፊንፊኔ በመገኘት ኢሬቻውን በአንድነት አክብረዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች ውብና ማራኪ በሆኑ ባህላዊ አልባሳትና እሴቶች አሸብርቀው፣ ባህላዊ ጭፈራዎችን ልዩ ልዩ ዜማዎችን በማዜም በዓሉን አክብረዋል።
የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የእርቅና የይቅርታ በዓል ነው።