ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በምን ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ?
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት፤ ለሶማሊያ ሰላም ከበድ መስዋዕትነት ለከፈሉ “የኢትዮጵያ መከላከያ ጀግኖች” ያላቸውን ክብር ገልጸዋል
የኢትዮጵያና ሶማሊያ መሪዎች የጸጥታው ም/ቤት በሞቃዲሾ ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲያነሳ የቀረበውን ጥያቄ እንዲያጤን ጠይቀዋል
የሶማሊያ ፕሬዝዳት ሀሰን ሼክ መሃመድ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ ሞቃዲሾ ተመልሰዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከበርካታ የሀገሪቱ የሀገሪቱ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት ሁለቱም ሀገራት አብረው ለመስራት በሚችሉባቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ በተለይም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ውይይት በተለያዩ አንኳር ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውነ ከሰዓታት በፊት በወጣው የጋራ መግለጫ ላይ ተመላክቷል።
መሪዎቹ በዚህም የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በሞቃዲሾ ከ30 ዓመታት በላይ ተጥሎ የቆየው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲነሳ በሶማሊያ መንግስት የቀረበው ጥያቄ እንዲያጤን ጠይቀዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀቡን ካነሳ ሶማሊያ ከሀገሪቱ አልፎ የቀጠናው ስጋት የሆነው አልሻባብን በብቃት ለመመከት የሚያስችል አቅም ይኖራታልም ነው ያሉት መሪዎቹ።
የጋራ ጠላታቸውን፣ ሽብርተኝነትንና ጽንፈኝነትን በመዋጋት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተባበር ያላቸውን ቁርጠኝነት የገለጹት መሪዎቹ፤ በጸጥታ ተቋሞቻው መካከል ትብብርና የመረጃ ልውውጥ ለማድረግም ተስማምተዋል።
ሁለቱም መሪዎች በቅርቡ የሶማሊያ ጦር በሂራን እና ጋልሙድ ክልሎች በአልሸባብ ላይ የሰነዘረው የተሳካ ጥቃትም አድንቀዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት፤ ላለፉት አስርት ዓመታት ለሶማሊያ ሰላም ከበድ መስዋዕትነት ለከፈሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ጀግኖች ያላቸው ክብርም ገልጸዋል።
ከፖለቲካና ጸጥታ ትብብር በተጨማሪ በንግድ፣ በኢኮኖሚና በመሰረተ ልማት እንዲሁም በኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዙሪያ ያለውን ትብብር ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን ሁለቱ መሪዎች አጽንኦት ሰጥተው መክረዋል።
መሪዎቹ፤ የየመንግስት መስሪያ ቤቶች የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ በተፈራረቀ መልኩ እንዲያካሂዱ፣በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው አቅጣጫዎችና ማስፈጸሚያ ዘዴዎችን እንዲያዘጋጁም አቅጣጫ አስቀምጠል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሁለቱ ሀገራት የክፍለ አህጉሩ ተደጋጋሚ ድርቅና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የተፈጥሮ አደጋዎች በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተጋፈጡ እንደሆነና የአከባቢውን ህዝቦች ህልውና አደጋ ላይ መውደቃቸንም አውስተዋል።
በዚህ ረገድ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን እና እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው መክረዋል።
በተጨማሪም መሪዎቹ ዓለም አቀፍ አጋሮች የተጎዱ ማህበረሰቦችን የረጅም ጊዜ ኑሮን የመቋቋም አቅምን በመገንባት ላይ ጨምሮ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የሰማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ላለፉት ሁለት ቀናት በኢትዮጵያ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ከሰአታት በፊት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።