የኢሬቻ በዓልን ለመረበሽ የተዘጋጁ ከ500 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
ስለተያዙት ግለሰቦች እና ስለተያዙበት ስፍራ የተገለጸ ዝርዝር መረጃ የለም
የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንም መያዙን የኦሮሚያ ፖሊስ ገልጿል
የኢሬቻ በዓልን ለመረበሽ የተዘጋጁ ከ500 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
መስከረም 23 እና 24 የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ለመረበሽ የተዘጋጁ 503 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ኮማንደር አራርሳ መርዳሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት፣ የኢሬቻ በዓል ላይ የሚሳተፉ የበዓሉ ታዳሚዎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ኮሚሽኑ በጥብቅ እየሰራ ነው።
በህዝባዊው የኢሬቻ በዓል ላይ የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት በተለያየ አቅጣጫ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሀይሎች እንዳሉ ኮሚሽኑ መረጃ እንደደረሰው ኮሚሽነሩ ኮማንደ አራርሳ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ድረስ 503 ሰዎች፣14 ክላሽ ፣ 26 ቦምብ እና 103 ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው የኢሬቻ በዓል በኮሮና ምክንያት እንደ ከዚህ ቀደሙ በርከት ያለ ሰው በተገኘበት የማይከበር ሲሆን በገዳ አባቶች የተላለፈውን ውሳኔ ህብረተሰቡ ስራ ላይ ማዋል እንዳለበትም ጄኔራል ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን “ኦሮሚያን የጦርነት አውድማ” ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሀይሎችን በማጋለጥ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ከመስከረም 25 በኋላ መንግስት የለም” እያሉ ህብረተሰቡን ለማወክ የሚፈልጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ኮማንደሩ ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ የህዝቡን ሰላም የሚያውኩትን በመከታተል ህግ ለማስከበር በቁርጠኝነት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡
በኢሬቻ በዓል ላይ ረብሽ ለመፍጠር አስበዋል በሚል ስለተያዙት ሰዎች ማንነት እና ስለተያዙበት ቦታ በዘገባው የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡