እውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግስት አቶ አሻድሊ እንዳሉት አቃፊ ነውን?
ዜጎችን ”መሥራችና ባለቤት” እና ”መጤ” ብለው የመደቡ የክልሎች ሕገ መንግስታት አሉ
የክልሎች ህገመንግስታት መነሻቸው ከሆነው የፌደራሉ ህገመንግስት እንዴት እንደሚቃረኑ የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ
የክልሎች ህገመንግስታት መነሻቸው ከሆነው የፌደራሉ ህገመንግስት እንዴት እንደሚቃረኑ የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግስት አንቀጽ 2 የክልሉ ባለቤት ብሔረሰቦች በሚለው ስር በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች የሚታወቁ ቢሆንም “የክልሉ ባለቤት ብሔር፣ ብሔረሰቦች በርታ፣ጉሙዝ፣ሽናሻ፣ማኦ እና ኮሞ ናቸው”ሲል ይገልጻል፡፡
ይህ አገላለጽ በክልሉ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ያገለለ ስለመሆኑ ምሁራን ያነሳሉ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ትናትና ከአማራ ክልል መንግስት አቻቸው ጋር ስለመተከል ግድያዎች በሰጡት መግለጫ እርሳቸው የሚመሩት ክልል ሕገ መንግስት አቃፊ አንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በተፈጠረው ግጭት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ የአማራና አገው ነዋሪዎች የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን የአማራ ክልል መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡ የአማራ ክልል መንግስት ጥቃት ሊደርስባቸው የቻለው በቂ ውክልና ስለሌላቸው ነው፤በመሆኑም ጥቃቱን ለመከላከል የአማራ ተወላጆች ከክልል እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች መሳተፍ አለባቸው ብሎ ነበር፡፡
ይልቁንም በክልሉ መተከል ዞን እየተፈጠሩ ላሉ ግድያዎች ተጠያቂው ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የሕግ ባለሙያዎች ግን የክልሉ ሕገ መንግስት አቃፊ ሳይሆን አግላይ አንደሆነ ማሳያዎችን በማጣቀስ ይሞግታሉ፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ ስሜ የክልሉ ሕገ መንግስት አቃፍ አይደለም ይልቁንም በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦችን የሚያገል ነው ይላሉ፡፡
አንቀጽ 39 የሚል መጽሐፍ የጻፈው የሕግ ባለሙያና አማካሪ አቶ ዉብሸት ሙላት ”መሥራችና ባለቤት”እና ”መጤ ”፤ ”የብሔረሰቦች ግንኙት ከሕገ መንግሥቱ አንጻር” በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሑፍ ላይ የጋምቤላ ክልል ሕገ መንግሥት በክልሉ የሚገኙትን ነባር ብሔር፣ ብሔረሰቦች ”መሥራች አባላት” በማለት ሲጠራቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ”የክልሉ ባለቤት ብሔረሰቦች” የሚሉ ሐረጋትን እንደሚጠቀሙ ይገልጻል፡፡
ከእነዚህ ሕግጋተ መንግሥታት መረዳት የሚቻለው መሥራች ያልሆኑና ባለቤት ያልሆኑ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዳሉ መሆኑን ገልጿል፡፡በተለይ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና የሐረሪ ክልሎች ካላቸው የብሔረሰቦች ስብጥር አንጻር ሲታይ ከእንደገና መጤን ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የሚያነሳው አቶ ውብሸት ለዚህም ህዝብ ቆጠራን ማንሳት እንደማሳያ ይሆናል ይላል፡፡
በ1999 ዓ.ም ከተደረገው አገር ሀቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት በቆጠራው መሠረት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላላ ነዋሪ ብዛቱ 784,345 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በርታ 199,303፣ አማራ 170,132፣ ጉሙዝ 163,781፣ ኦሮሞ 106,273፣ ሽናሻ 60,587፣ ማኦ 15,384፣ ኮሞ 7,773፣ ትግራዋይ 5,562 ሲሆኑ ከዚህ በታች ቁጥር ያላቸውም እንዳሉ አቶ ውብሸት ያነሳል፡፡
ይሁን እንጂ የክልሉ ባለቤት ብሔረሰቦች ተብለው ዕውቅና የተሰጣቸው በርታ፣ጉሙዝ፣ሺናሻ፣ማኦና ኮሞ መሆናቸውን እና ሕገ መንግስቱ አብላጫ ቁጥር ያላቸውን ማግለሉን ያነሳል፡፡
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተጠቀሙበትን አጻጻፍ ከዓለምአቀፉ አረዳድ ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ አቶ ውብሸት ይናገራል፡
በክልል ሕገ መንግስታት ውስጥ የተወሰኑትን መሥራችና ባለቤት ወይም ነባር ሌሎችን ደግሞ መጤ ማለት አልበለዚያም የመጤነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ የጋራ ሀገር ግንባታ ላይ በጎ ሚና ሊጫወት እንደማይችል አቶ ውብሸት ይገልጻል፡፡
”ነባርነትና መጤነት የፖለቲካ መቆራቆሻ ነው፤ጥል አንጋሽ ነው” የሚለው አቶ ውብሸት በተለይም ነባሩ መሬቱንና ሀገሩን ከደሙ ጋር በማያያዝ እናት ሀገሬ ወይንም አባት ሀገሬ፣ እትብቴ የተቀበረበት መንደሬ ወይም ቀዬዬ በማለት ሲጠራና ለልጅ ልጅ ለማስተላለፍ ሌሎች እንዳይነጥቁት ሲታገል እንደሚስተዋል ያነሳል፡፡ በዚህ ትግል መካከል የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እንደሚከሰቱና የኢትዮጵያ ችግርም ይህ እንደሆነ ይነሳል፡፡
አቶ ኤርሚያስ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግስትን ጨምሮ የሌሎች ክልሎች ሕገ መንግስቶች አግላይና ከፋፋይ በመሆናቸው በአስቸኳይ ሊቀየሩ እንደሚገባ ነው የገለጸው፡፡
የከተማ ምክር ቤቶች ምርጫን በተመለከተ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የከተሞች ማዕከላትን ለማቋቋምና ሥልጣናቸውን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ላይ እንደተገለጸው ለከተማ ምክር ቤት በሚደረደግ ምርጫ ከምክር ቤቱ መቀመጫ ውስጥ 55 በመቶው ለክልሉ ነባር ሕዝቦች የተተወ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
የክልል ህገመንግስታት ከፌደራል ህገመንግስት እንዴት ይቃረናሉ?
የሀገሪቱ ሕገ መንግስት አንቀጽ 25 “ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፣ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው” ቢልም ይህ ግን በቀጥታ ከክልሎቹ ሕገ መንግስት ጋር እንደሚቃረን የሕግ ባለሙዎቹ ያነሳሉ፡፡
በሌላ በኩል የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 32 ንዑስ ንዑስ አንቀጽ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነጻነት አለው” ይላል፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ ስሜ ታዲያ የክልል ሕገ መንግስቶች ሙሉ ለሙሉ ከሀገሪቱ ሕገ መንግስት ጋር የሚጣረሱ እንደሆኑ ነው የገለጸው፡፡
በሌላ መልኩ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 38 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት በቀጥታ እና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳ ደር የመሳተፍ፣ ዕድሜው 18 ዓመት ሲሞላ በሕግ መሰረት የመምረጥ መብቶች እንዳሉት ቢደነግግም ይህ ግን በክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን ነው አቶ ኤርሚያስ የሚገልጸው፡፡
በመሆኑም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሕገ መንግስቱ አቃፊ ነው ማለታቸው ትክክል እንዳልሆነ ነው የሕግ ባለሙዎቹ ያስረዱት፡፡ በአጠቃላይ የክልል ሕገ መንግስቶች ከፌዴራሉ ሕገ መንግስት ጋር የተቃረኑ እንደሆኑ ባለሙያዎቹ አብራርተዋል፡፡