የፍ/ቤት ትእዛዝ አለመፈጸምና ያስከተለው ትችት
በፍርድ ቤት ክርክር ፖሊስ እንደ አንድ ተከራካሪ በመሆኑ እንደ ተከራካሪ መታየት አለበት-የህግ ባለሙያ አቶ ሞላልኝ
የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዘዳንት ወ/ሮ መአዛ ቃለመሃላ ሲፈጽሙ ፍ/ቤቶች አጥተዋል ያሉትን ተዓማኒነት ለመመለስ ቃል ገበተው ነበር
የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዘዳንት ወ/ሮ መአዛ ቃለመሃላ ሲፈጽሙ ፍ/ቤቶች አጥተዋል ያሉትን ተዓማኒነት ለመመለስ ቃል ገበተው ነበር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመንግስት መሪ ሆነው ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ ቀደም ሲል የተዓማኒነትና የገለልተኝነት ጥያቄ ሲነሳባቸው ለነበሩት የዴሞክራሲ ተቋማት የሰጧቸው ሹመቶች በብዙሃኑን ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡
በተለይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት በመሆን የተሸሙት መአዛ አሸናፊ በአቅም ማነስና በተዓማኒነት ችግር ሲታማ የነበረውን የህግ ተርጓሚ አካል ያስተካክሉታል የሚል ግምት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡
ወ/ሮ መዓዛ በሹመታቸው ዕለት “ቀደም ሲል በሕግ አምላክ ሲባል ሰው የሕግን ዋጋ ያውቃል፣ ይህ እምነት እንዲመለስ እሰራለሁ፣ በጥቅሉ ሕግ የበላይ እንዲሆን እሰራለሁ“ ብለው ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡
ነገርግን ፍረድቤቶች አሁንም አቅም የላቸውም፤ በህግ አስፈጻሚ ስር ወድቀዋል የሚል በተለይም ከፖለቲካ ፓርቲ ሰዎች ትችት እየተሰማ ይገኛል፡፡
የፍርድ ቤቶች የበላይነት እየተሸረሸረ ነው ለሚለው ትችት በርካታ ማሳያዎች ይነሳሉ፡፡
ለአብነትም የአሥራት ሚዲያ ሀውስ ባልደረቦች ፍርድ ቤት ለእያንዳንዳቸው የ10ሺ ብር ዋስትና ቢፈቅድም ፖሊስ ግን ለመፍታት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ በፖሊስና በፍርድ ቤቶች መካከል ያለው የሥራ ግንኙነት ሕገ መንግስታዊ አይደለምን አስብሏል፡፡
በተመሳሳይ የኢዴፓ ብሔራዊ ኮሚቴ አባል አቶ ልደቱ አያሌው በምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢከሰሱም ፍርድ ቤቱ የአቃቢ ህግንና የጠበቆቻችንን የህግ ክርከር መርምሮ በ100ሺ ብር ዋስትና ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ወስኖ ነበር፡፡
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ አሁን ላይ ይህ የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበር የሚያሳየው የፍትህ ስርዓቱ ላይ የበዛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መኖሩ ነው ብለዋል፡፡
የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለአቶ ልደቱ የተፈቀደው ዋስትና ተግባራዊ አለመደረጉን ተከትሎ በችሎቱ ላይ “ጦር ሰራዊት ቢኖረን አዘን ልከን እናስፈታህ” ነበር ማለቱን አቶ አዳነ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ምክትል መሪ አቶ አንዱአለም አራጌ በበኩላቸው በቅርቡ የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ አባል ወይዘሮ ሂሩት ክፍሌ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቷን እንዳከበረላት ገልጸው ፓሊስ ላለመልቀቅ ወስኖ ነበር ይላሉ፡፡
አቶ አንዱአለም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ለአቶ ልደቱ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ ቢያዙም በፓሊስ እንቢተኝነት ግን በእስር ላይ መሆናቸውን ገልጸው ይህ ለምን ሆነ ብለው ይጠይቃሉ፡፡
የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ፍርድ ቤቶች ዋስትና ፈቅደው ፖሊስ አልፈጽምም ማለቱን ተከትሎ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት መዓዛ አሸናፊ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡
የኢዜማ ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤቱ የፈቀደላቸውን ዋስትና መከልከላቸውን በተመለከተ አቶ ልደቱ ትክክል አይደለም፣ ህገወጥ ነው ብለው ወደህግ ፊት ያቀረቡት ሰዎች የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ የማያከብሩና የራሳቸውን ስሜት የሚተገብሩ ከሆነ መጀመሪያውኑ ለምን ዳኛ ፊት አቀረቡት? በማለት አቶ ልደቱ ፍርድ ቤቱ የፈቀደላቸው የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸውና ሕግ ተርጓሚው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡
የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ሞላልኝ መለሰ ችግሩ ያለው ራሳቸው ፍርድ ቤቶቹ ላይ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡እንደ አቶ ሞላልኝ ገለጻ ፍርድ ቤት ክርክር ላይ ፖሊስ መታየት ያለበት እንደ አንድ ተከራካሪ በመሆኑ ከተከራካሪ በላ መታየት እንደሌለበት ያነሳሉ፡፡
ተጠርጣሪው መለቀቅ እንደሚፈልግ ሁሉ ፖሊስም ተከራካሪ ስለሆነ አለመለቀቅን ይፈልጋል ያሉት ጠበቃና የሕግ አማካሪው ፖሊስ ምንም እንኳን በሕግ የተቋቋመ ቢሆንም ፍርድ ቤት ላይ ተከራካሪ የመሆን ባህሪው ግን እንደማይለወጥ ነው የሚነሱት፡፡
ፍርድ ቤት ዋስትና ከሰጠ እና የበላይ ፍርድ ቤት ካልሻረው ማንም ምድራዊ ኃይል ይህንን መሻር እንደማይችል ያነሳሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች ዋስትና ከፈቀዱ በኋላ ተጠርጣሪዎች ወደ ማረፊያ ቤት መመለስ እንደሌለባቸው የሚያነሱት ባለሙያው ይህ መሆን የሌለበት ነገር ግን እንደ ባህል የተቆጠረ አስነዋሪ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ፍርድ ቤት እንዲለቀቅ የወሰነውን ውሳኔ ባለማክበር ፖሊስ አለቅም ካለ ፍርድ ቤቱ እዛው አቁሞ ተጠርጣዎቹ እንዲፈቱ ማድረግ አለበት እንጅ ፖሊስ ያልፈታበትን ምክንያት ቀርቦ ያስረዳ እየተባለ ቀጠሮ መስጠት ትክክል እንዳልሆነ አቶ ሞላልኝ አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ሞላልኝ ገለጻ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍርድ ቤት ዋስትና ፈቅዶ ፖሊስ አልፈታም የሚልበት መንገድ ችግሩ የፖሊስ ሳይሆን የፍርድ ቤቶች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ተጠርጣሪዎችን ይዞ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጣው ፖሊስ እንደ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ ዋስትና ሲሰጥ ሃላፊዎች ጋር ሄዶ ተናግሮ ከዛ ሃላፊው በሚያዘው መሰረት የሚደረገው ሂደት ትክክል እንዳልሆነ ነው ባለሙያው የሚያነሱት፡፡
በመሆኑም ፍርድ ቤቶች ራሳቸው የፈቷቸው ሰዎች መልሰው እንዲታሰሩ ያደረጉት ራሳቸው ፍርድ ቤቶች መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ሞላለት ፍርድ ቤቶች ራሳቸው የሰጡትን ውሳኔ እዛው ፍርድ ቤት አስፈጽመው መውጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡