በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ በማጋጠማቸው ፈጣን ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል ተባለ
በክልሉ ከዚህ ቀደምም ብዙዎች ህይወታቸውን ያጡበት ተደጋጋሚ ጥቃት ተፈጽሟል
”ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሳሳቢ መረጃዎች ደርሰውኛል”-ኢሰመኮ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ በማጋጠማቸው ፈጣን ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል ተባለ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሰሞኑ በተፈጸመ ጥቃት ከ80 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን የተለያዩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ ማንነትን መሰረት አድርጎ መፈጸሙንም ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡ ከአሁን ቀደም በአካባቢው ተደጋግመው በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች መገደላቸውና መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ አውጥቷል፡፡
በክልሉ ከሰሞኑ በሁለት ዙር በደረሱ ጥቃቶች ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸውን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ነው ኢሰመኮ ያስታወቀው፡፡ ኮሚሽኑ ከክልሉ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ እንዲሁም ከወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን ገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ ከጳጉሜ አንድ ጀምሮ ባለፉት ጥቂት ቀናት ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግስት ማረጋጡን ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ እንዳሳሰቡት ገልጾ በክልሉ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን እንደሚያወግዝ ነው ያስታወቀው፡፡
በሀገሪቱ ሕገ መንግስትና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ማለትም በአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ በዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የሰብአዊ መብቶት ሰነዶች የተደነገጉት በሕይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ አሳስቧል ኮሚሽኑ፡፡
ኮሚሽኑ በክልሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ምርመራዎችን በማካሄድ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡም አሳስቧል፡፡
የሚመለከታቸው የክልሉ መንግስት አካላት ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀደመ ህይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻቹ እንዲሁም መሰረታዊ የሆነው በህይወት የመኖር መብት ይረጋገጥ ዘንድ የሚመለከታቸው የክልሉ የመንግስት አካላት እንዲሰሩም አሳስቧል፡፡
በመጨረሻም ኮሚሽኑ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች እና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉ እና ከማንኛውም ዓይነት የሁከት ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡