ሞሮኮ ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር በመሆን የ2030 የዓለም ዋንጫን የማዘጋጀት እቅድ አላት
ሞሮኮ የዓለማችን ግዙፍ ስታዲየም ግንባታ ዲዛይን ይፋ አደረገች።
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ የ2030ን ፊፋ ዓለም ዋንጫ ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር በቅንጅት የማዘጋጀት እቅድ አላት።
48 ብሔራዊ ቡድኖች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀው ይህ የዓለም ዋንጫ በ20 ስታዲየሞች እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ስፔን ለዚህ ውድድር 11 ስታዲየሞችን እንደምታዘጋጅ ስትገልጽ ቾርቹጋል ሶስት እንዲሁም ሞሮኮ ደግሞ ስድስት ስታዲየሞችን እንደሚያዘጋጁ አስታውቀዋል።
ሞሮኮ ለዚህ ውድድር ከምታዘጋጃቸው ስድስት ስታዲየሞች መካከል አንዱ "ሀሰን ሁለተኛ" የተሰኘ ስታዲየም የግንባታ ዲዛይን ይፋ አድርጋለች።
ይህ ስታዲየም ሲጠናቀቅ 115 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል የተባለ ሲሆን በግዝፈቱ ከዓለም ትልቁ እንደሚሆን ተገልጿል።
የሞሮኮ ብዙሀን መገናኛዎች እንደዘገቡት ከሆነ አዲሱ ስታዲየም ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ካዛብላንካ 38 ኪሎ ሜትር ላይ ይገነባል።
በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ግንባታው ይጀምራል የተባለው ይህ ስታዲየም በ2028 ይጠናቀቃል ተብሏል።
ዓለም አቀፉ የስፖርት ፌዴሬሽን ወይም ፊፋ የ2030 ዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ ሀገራትን እስካሁን በይፋ አላሳወቀም።
ውድድሩን ለማዘጋጀት እየተፎካከሩ ካሉ ሀገራት መካከል ሞሮኮ፣ ስፔን እና ፖርቹጋል እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።
ይሁንና ሶስቱ ሀገራት የፍጻሜውን ውድድር ማን ያስተናግድ የሚለውን እስካሁን አልተስማሙም።