የዩክሬን ጦርነት ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ሲል ተመድ አስጠነቀቀ
ተመድ በተወሰኑ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ረሃብ ሊከሰት ይችላል ብሏል
የዓለም የምግብ ዋጋ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ለዓመታት የሚዘልቅ አቀፍ የምግብ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በሰጡት መግለጫ፤ ጦርነቱ በተለይም በደሃ ሀገራ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን አዳጋች እያደረገው አንደሆነ ተናግረዋል።
- ሩሲያ ወደ ውጭ በምትልከው ስንዴ ላይ በታሪክ ከፍተኛ የተባለ የታክስ ጭማሪ አደረገች
ዩክሬን ወደ ውጭ ሀገራት የምትልካቸው የምግብ ፍጆታ ምርቶች ከጦርነቱ በፊት ወደነበረው የማይመለስ ከሆነም በተወሰኑ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችልም አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ከዩክሬን በስፋት ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ የነበሩ እንደ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ እና በቆሎ ያሉ ምርቶችን ስርጭት እንዲቆም ማደረጉንም ጉቴሬስ ተናግረዋል።
ይህም ዓለም አቀፍ የምግብ አቅርቦት እንዲቀንስ እና በዓለም ገበያ ያለው የምግብ ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉንም አስታውቀዋል።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ ጭማሪ ማድረጉን ያሳያል።
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በኒው ዮርክ ባደረጉት ንግግር፤ በዓለም ሀገራት ያለው ግጭት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተደምሮ በ10 ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለምግብ ዋስትና ችግር እየዳረገ ነው ብለዋል።
“በጋራ መቆም ከቻልን ለዓለም በቂ ምግብ አለ” ያሉት አንቶኒዮ ጉቴሬስ፤ ችግሩን በጋራ መቅረፍ ካቻልን ግን በወራት ውስጥ ዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል ሲሉም ተናገረዋል።
ለዚህም ብቸኛው መፍትሄ የዩክሬን የምግብ ምርትን ወደነበረበት መመለስ እንዲሁም በሩሲያ እና በቤላሩስ የሚመረቱ ማዳበሪያዎችን ወደ ዓለም አቀፉ ገበያ ተመልሰው እንዲገቡ ማድረግ ነው ብለዋል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር (ኔቶ) አቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገባች ሶስት ወር ሊሞላት ጥቂት ቀናት ቀርቷታል።
የዓለማችን ቀዳሚ የስንዴ አምራች እና ላኪ የሆኑት ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት ማምራታቸው በዓለም የምግብ ዋጋ እንዲንር አድርጓል።
ጦርነቱን ተከትሎም በርካታ የስንዴ አምራች ሀገራት የስንዴ ንግዳቸውን በመከለስ ላይ ሲሆኑ ሕንድም ባለፍነው ሳምንት በሀገሯ የሚመረት ስንዴ ወደ ውጭ ሀገራ እንዳይወጣ እገዳ መጣሏ ይታወሳል።
የሩሲያ መንግስትም ባሳለፍነው ወር ወደ ውጭ በሚላከው ስንዴ ላይ የታክስ ጭማሪ ማደረጉን የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም።
ሚኒስቴሩ፤ ከሀገሪቱ ወደ ውጭ በሚላክ ስንዴ ላይ የታክስ ጭማሪ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት አንድ ቶን ስንዴ ወደ ውጭ ሲላክ 101 ነጥብ 4 ዶላር እንዲከፈል መንግስት ወስኗል።