የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዕውን የሕገ መንግስቱ መታሰቢያ ነው?
አንድ ምሁር የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት ”በአፍሪካ 80 ሀገር ለመጨመር የሚፈልግ ሰነድ” ሲሉ ይገልጻሉ
በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የሚያደንቁም የሚተቹም ብዙዎች ናቸው፡፡ በዓሉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያዘጋጅና የሚያስተባብር ሲሆን ክልሎችም ወረፋ በመያዝ ያከብሩታል፡፡ በየዓመቱ ሕዳር 29 ቀን የሚከበረው ይህ ዕለት በበርካቶች የብሔር ብሔረሰቦች ዋስትና ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አንዳንዶች ግን የሀገሪቱን አንድነት ከማጉላት ይልቅ ልዩነትን ያመጣል በሚል ከፍተኛ ወቀሳ ይሰነዝሩበታል፡፡ ይህንን በተመለከተ አሁን በኢትዮጵያ መንግስት በሕግ ቁጥጥር ስር ያሉት የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም ፣ ከዓመት በፊት ሕዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር የብሔር ብሔረሰቦች በአል “ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን ያጎላል” መባሉ ዕለቱን ለማሳነስ ያለመና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
በእርግጥ በበዓሉ የተለያዩ አካላት በአደባባይ ለመተዋወቅና ለመገናኘት ዕድል ያገኛሉ በማለት በጎ ጎኑን የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና የማህበረሰብ አንቂው ሙክታቪች ኡስማኖቫ በቅድሚያ ማነው ብሔር? ማነው ብሔረሰብ? ማነው ህዝብ? የሚለው ሕብረተሰቡን አላግባባም ይላሉ፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላትም እንዲሁ "ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ" ሦስት ቃላት እንጂ አንድ ትርጉም ብቻ ያለው ሐረግ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ የሶስቱ ልዩነት በማብራሪያው አለመዘርዘሩን የገለጹት ባለሙያው በደፈናው ግን "የመጠንና ስፋት" ልዩነት እንዳላቸው ያስቀምጣል፡፡
ለአብነትም በአማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩትን በተመለከተ አማራን "ብሔር"፣ አገውን "ብሔረሰብ" እንዲሁም ኦሮሞን "ሕዝብ" በማለት በአንቀጹ ማብራሪያ ሠነድ ላይ በመግለጽ በሦስቱ መካከል የመጠንና የስፋት ልዩነት እንዳላቸው ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን በጠቅላላው እንደምሳሌ ኦሮሞን "ብሔር"፣ አፋርን "ብሔረሰብ"፣ ኩሎን "ሕዝብ" በማለትም መቀመጡ "የመጠንና ስፋት" ልዩነት እንዳለ ያሳያል ይላሉ፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝብም የየራሳቸው ትርጉሞች እንዳሏቸው ገልጸው የአሁኑ ሕገ መንግስት ግን ሦስቱን ቃላት አንድ ላይ ሰብስቦ የኢትዮጵያን ነገር ቸል ብሎ ስታሊናዊ ብያኔ ይሰጠዋል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ለሦስቱም አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም ተሰጥቷቸዋል የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው በሕገ መንግስቱ ላይ የጋራ ጠባይ የሚለው ለግለሰብ እንጂ ለብሔር የምንጠቀምበት መሆን አልነበረበትም ይላሉ፡፡
አቶ ውብሸት ''ብሔርን በታሪክ ሂደት ውስጥ የተከሰተ የሰዎች ስብስብ ነው'' የሚለውን የሶቪየቶች ሀሳብ በመጥቀስ በአንድ መልክአ ምድራዊ ክልል ውስጥ መኖር በኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፣ በአንድ ቋንቋ መጠቀም በጋራ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ የወል ሥነ-ልቦናዊ ገጽታዎችና ባህላዊ አመለካቶች መከሰት የብሔር መሠረቶች እንደሆኑ ያብራራሉ፡፡ በጥቅሉ አንድ ብሔር በመጀመሪያ ደረጃ የሚለየው ባሉት የወል፣ቁሳዊና የኑሮ ሁኔታዎች እንደሆነ አቶ ውብሸት ይጠቅሳል፡፡ የሕገ መንግስቱ መግቢያ ስለአብሮነት እየሰበከና ዕጣ ፈንታችን አንድ ነው እያለ እንዲሁም የአብሮነት ጋብቻን እያበሰረ አንቀጽ 39 ላይ ሲደርስ ግን እስከ መገንጠል ብሎ ድንጋጌ ማስቀመጡ ለሀገራዊ አንድነት ከፍተኛ ዕንቅፋት ይሆናል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
ከዓመት በፊት ወ/ሮ ኬሪያ የሕገ መግስቱንና የበዓሉን አስፈላጊነት በአግባቡ መረዳት ካልተቻለ ስጋት እንደሆነ ሁሉ በአግባቡ ከተያዘ ደግሞ የአንድነት ማጠናከሪያ እንደሚሆን ቢገልጹም የተለያዩ ምሁራን ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ አቶ ሙክታሮቪች አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ”የደንቆሮ ስራ ሕገ መንግስት” ነው በማለት በአንቀፅ 39 ላይ ያላቸውን ቅሬታ ያነሳሉ፡፡
ለ 80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የመገንጠል መብት በመስጠት በአፍሪካ ላይ 80 ሀገር ለመጨመር የሚፈልግ ሰነድ እንጂ ፣ ሕገ መንግስቱ ሀገር ማለት ምን ማለት ነው ብለው በሚያስቡ ሰዎች የረቀቀ እንደማይስላቸውም ይናገራሉ፡፡ አቶ ሙክታሮቪች የሕገ መነግስቱ አንቀጽ 39 የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን መነሻ በማድረግ ”ሰው እንዴት በጋብቻው ቀን የፍቺ ውልን አብሮ ይፈርማል?” ብለው በመጠየቅ ”ለመፋታት እያቀዱ የመጋባት ግራመጋባት” ይሉና ፣ ”መቼም ቼክ ተሰጥቶህ አትመንዝር፣ ስጋ ተሰጥቶህ ቢላዋውን አታንሳ አትባልም” ሲሉ ይገልጹታል፡፡
በአጠቃላይ በዓሉና ሕገ መንግስቱ የምሁራንና የፖለቲከኞች ብሎም የአክቲቪስቶች የመከራከሪያ አጀንዳ ከሆነ ቆየት ብሏል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ በዓሉን በአደባባይ እያከበረች ነው፡፡