በዓሉ ሕወሓት ሕልውናውን ለማጣት በተቃረበበት ወቅት የተከበረ የመጀመሪያው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ነው
ምንም እንኳን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የቀድሞ ድምቀቱን ባይላበስም 15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሕገ መንግሥቱ ተግባር ላይ በዋለበት ዕለት ዛሬ ሕዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም ተከብሮ ውሏል፡፡
በዓሉ ሕገ መንግሥቱን ማዘጋጀትን ጨምሮ ከ2 ዓመት ተኩል በፊት ሀገራዊ ለውጥ እውን ከመሆኑ በፊት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለ27 ዓመታት የበላይነት የነበረው ሕወሓት ከስልጣኑ ከመውረዱ ባለፈ ሕልውናውንም ለማጣት በተቃረበበት ወቅት የተከበረ የመጀመሪያው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ነው፡፡ ም/ጠ/ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንንም በአዲስ አበባ በነበረው የበዓሉ ሲምፖዚየም ላይ ያስተጋቡት ይሄንኑ ነው፡፡
የበዓሉ አከባበር ምን ይመስላል?
በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻው መጠናቀቁን የገለጸው የፌዴራል መንግሥት በቀጣይነት በወንጀል የሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮችን እና ከመከላከያ ሠራዊት የከዱ አመራሮችን የማደን ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባኤ የነበሩት ኬሪያ ኢብራሂም እና የትግራይ ክልል የቀድሞ ም/ር/መስተዳድር የነበሩት አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡ በወንጀል የሚፈለጉ ሌሎች አመራሮች ይገኙበታል የተባለው ስፍራ በመከላከያ ሠራዊት ተከቦ እንደሚገኝም ነው መንግሥት ይፋ ያደረገው፡፡