አምባሳደር አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር) በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
የተመድ ሰራተኞች ያልተፈቀዱ ኬላዎችን አልፈው ሲሄዱ መንግሥት እንደተቆጣጠራቸውም ተናግረዋል
የቀሩት የሕወሓት አመራሮች በጥቂት ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉም አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል
የቀድሞው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር) በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ሴክሬታሪያት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባዔ የነበሩት ኬሪያ ኢብራሂምም በቅርቡ እጅ መስጠታቸውን ያስታወሱት አምባሳደር ሬድዋን ሌሎች በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በመንግሥት ኃይል እየታደኑ የሚገኙት የቀሩት የሕወሓት አመራሮች በጥቂት ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉም አምባሳደር ሬድዋን ዛሬ ለውጭ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድርጅት ሰራተኞች ያልተፈቀዱ ሁለት ኬላዎችን አልፈው ሲሄዱ የተወሰኑት ተተኩሶባቸው እና ተይዘው በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡ በቁጥጥር ስር የዋሉት አሁን ላይ መለቀቃቸውን የገለጹ ሲሆን የተለያዩ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድርጅቶች በትግራይ ክልል የሚያከናውኑትን ስራ ከመንግሥት ጋር ተናበው የመስራት ግዴታ እንዳለባቸው በተደረሰው ስምምነት መሰረት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ራሳቸውም ለአደጋ እንዳይጋለጡ የተመድ ሰራተኞች ሰላማዊ ከሆኑ ስፍራዎች አልፈው መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው መክረዋል፡፡
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በነበሩት ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ቢሮ የተገኘው ዋሻ የሕወሓት ቡድን በፌዴራል መንግሥት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ለረዥም ጊዜያት ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር የሚያሳይ መሆኑንም ነው አምባሳደር ሬድዋን የገለጹት፡፡
በትግራይ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፎች ከ10 የተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን በቅንጅት እየተደረጉ መሆኑን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ገልጸዋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በሕወሓት ኃይል ጥቃት መፈጸሙ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ መቀሌን መቆጣጠሩ ይታወቃል፡፡ ሠራዊቱ መቐሌን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሠራዊቱ ንብረት የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በርካታ የሕወሓት የጦር መሳሪያዎችንም መቆጣጠሩን ገልጿል፡፡
የሕግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻው መጠናቀቁን የገለጸው የፌዴራል መንግሥት በቀጣይነት በወንጀል የሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮችን እና ከመከላከያ ሠራዊት የከዱ አመራሮችን የማደን ተግባር በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በወንጀል የሚፈለጉ አመራሮች ይገኙበታል የተባለው ስፍራ በመከላከያ ሠራዊት ተከቦ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የፌዴራል መንግሥትን እና ሕወሓትን ለማሸማገል ቢሞክሩም ከወንጀለኞች ጋር ለድርድር አልቀመጥም ያለው የፌዴራል መንግሥት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡