ፑቲን የሞስኮውን ጥቃት ተከትሎ ዛቻና ቁጣ በተቀላቀለበት ንግግራቸው ምን አሉ?
ፑቲን “ሩሲያ በጥቃቱ ላይ የተሳተፉትን ሁሉንም ለይታ ትቀጣለች” ብለዋል
በጥቃቱ ላይ ቀጥታ ተሳትፎ የነበራቸው አራት ሰዎች ወደ ዩክሬን በመሸሽ ላይ እያሉ ነው የተያዙት ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትናንት ምሽት በሞስኮ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ ዛሬ ንግግር አድርገዋል።
በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በተዘጋጀ የሙዚቃ ድግስ ላይ ታጣቂዎች ትናንት ምሽት ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ታጣቂዎቹ በአውቶማቲክ የጦር መሳሪያ እና በቦምብ ባደረሱት ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ130 የተሸገረ ሲሆን፤ የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ145 ማለፉ ነው የተነገረው።
ይህንን ተከትሎ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ሩሲያውያን ሀዘናቸው ገልጸዋል።
ነገ መጋቢት 15 በመላው ሩሲያ የሀዘን ቀን እንደሚሆን የገለጹት ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ “የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎቻችን ይዘከሩበታል” ብለዋል።
አሁን ላይ በጥቃቱ ላይ ቀጥታ ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጠር ስር መዋላቸውን ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ፤ ሌላ የጅምላ ግድያ እንዳይፈጸም የጸጥታ ኃሎች ሰፊ ስራ እየሰሩ ነው ብለዋል።
“በሞስኮ እና በሌሎች የሩሲያ ክልሎች ተጨማሪ የፀረ ሽብር እርምጃዎች እየተተገበሩ ናቸው” ያሉ ሲሆን፤ “በትናንትናው የሽብር ጥቃት ላይ የተሳተፈ እና ያገዛቸው የትኛውም አከል ለህግ ይቅርባል” ብለዋል።
በትናንትናው የሽብር ጥቃት ላይ የተሳተፉ 4 ወንጀለኞች ወደ ዩክሬን ሊያመልጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ፕሬዝዳንት ፑቲን አስታውቀዋል።
“አሁን ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያመላክተው በዩክሬን በኩል ሽብርተኞች ለማስመለጥ የሚያስችል መንገድ በድንበር በኩል ተዘጋጅቶ እንደነበረ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
“ሩሲያ በዚህ የሽብር ጥቃት ላይ የተሳተፉ ሁሉንም አካላት ለይታ ትቀጣለች” ያሉት ፑቲን፤ “ሽብርተኞችን የሚጠብቀው የበቀል እርምጃ ብቻ ነው፤ ከዚህ ውጪ ምንም አማራጭ እና ተስፋ የላቸውም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ለሩሲያውያን ባስተላለፉት መልእክትም፤ “አሁን የሚጠበቅባችሁ በአንድነት መቆም ብቻ ነው፤ የሩሲያን ዜጎች አንድነት ማንም ሊነቀንቀው አይችልም” ሲሉም ተናግረዋል።