ሩሲያ በሞስኮ ጥቃት የፈጸሙትን ሰዎች እያደነች ትገኛለች
በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በተዘጋጀ የሙዚቃ ድግስ ላይ ታጣቂዎች ትናንት ምሽት ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ታጣቂዎቹ በአውቶማቲክ የጦር መሳሪያ እና በቦምብ ባደረሱት ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ133 የተሸገረ ሲሆን፤ የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ100 ማለፉ ነው የተነገረው።
ስለ ጥቃቱ
ጥቃቱ የተፈጸመው ትናንት ማለትም አርብ ምሽት ላይ ሲሆን፤ በሞስኮ በሚገኘው ኮርኩስ ሲቲ ሆል አዳራሽ ውስጥ እየተካሄደ በነበረ የሙዚቃ ድግስ ላይ ነበር።
የጥይት መከላከያ ጃኬት የለበሱ አምስት የሚሆኑ ሰዎች የሙዚቃ ኮንሰርቱ ወደ ተዘጋጀበት ኮርኩስ ሲቲ ሆል በመግባት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውም ታውቋል።
በተጨማሪም ጥቃቱን የፈጸሙ ሰዎች የእጅ ቦምብ እና ሌሎች ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በመወርወር 12 ሺህ 900 ስኩዌር ሜትር የሚሸፍን የአዳራሹን ክፍል በእሳት ማጋየታቸውም ተነግሯል።
የሩሲያ መርማሪዎች ጥቃቱን ተከትሎ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ133 ማለፉን እና 100 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።
ጥቃት አድርሾቹን የማደን ስራ
የሩሲያ የምርመራ ኮሚቴ፤ ከፍተኛ የመንግስት የወንጀል ምርመራ ኤጀንሲ በጥቃቱ ላይ "የሽብር" ምርመራን ከፍቷል።
“ሮስግቫርዲያ” የሩሲያ ብሄራዊ ዘብ በሞስኮ የሙዚቃ ኮንሰርት ለይ ጥቃት ያደረሱ ሰዎችን የማፈላለግና የማደን ስራ ላይ ተሰማርቷል ተብሏል።
ሩሲያ በጥቃቱ ላይ ቀጥታ ተሳትፎ ያላቸውን 4 ሰዎች ጨምሮ እስካሁን 11 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውላች።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቤተ መንግስት ክሬምሊን በጥቃቱ ዙሪያ እስካሁን ተጠያቂ ያደረገው አካል የለም የተባለ ሲሆን፤ ሆኖም ግን የተወሰኑ የሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዩክሬንን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ መይክሃይሎ ፖዶልያክ፤ ዩክሬን በዚህ ተግባር ውስጥ እጇ የለበትም ሲሉ አስተባብለዋል።
“ዩክሬን የሽብር መንገድን ተጠቅማ አታውቅም” ያሉት አማካሪው፤ “በጦርነቱ ውስጥ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ መፍትሄ የሚያገኙት በጦር ግንባር ነው” ብለዋል።
ለጥቃቱ ማን ኃላፊነት ወሰደ?
በሽበርተኘት የተፈረጀው ኢስላሚክ ስቴት (አይ.ኤስ) ለጥቃቱ ኃላፊነት እንደሚወስድ ያስታወቀ ሲሆን፤ የአይ ኤስ ክንፍ የሆነው የአፍጋኒስታኑ የኮርሳን ፕሮቪንስ ኢስላሚክ ስቴት ጥቃቱን ያደረሱት አባላቱ እንደሆኑ ገልጿል።
አይ ኤስ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አጭር ማብራሪያ፤ ተዋጊዎቹ በሞስኮ ዳርቻ ላይ ጥቃት በመሰንዘር፣ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፣ አቁስለዋል፣ በቦታው ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሰዋል፤ ከዚያ አምልጠዋል” ብሏል።
ሩሲያ በዚህ ወር ብቻ ከአይ ኤስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በርካታ ጥቃት ሙከራዎችን እንደነበሩ እና በርካቶችን ማክሸፏን ስትገልጽ ቆይታለች።
አሜሪካም ባሳለፍነው ሳምንት ላይ ጽንፈኞች በሞስኮ የማይቀር የሽብር ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ በማለት ማስጠንቀቋ አይዘነጋም።