አሜሪካም መሪው በጥቅምት ወር አጋማሽ መገደሉን አውቅ ነበር ብላለች
የአይ ኤስ አይ ኤስ መሪ አቡ አል ሀሰን አል ቁራይሺ መገደሉን ቡድኑ ገልጿል።
የአይ ኤስ ቃል አቀባይ አቡ አል ሙሃጂር በለቀቀው አጭር የቪዲዬ መግለጫ ፥ የቡድኑ መሪ በቅርቡ በውጊያ ላይ እያለ መገደሉን ተናግሯል።
ቃል አቀባዩ ስለአሟሟቱ ግን ዝርዝር መረጃን አልሰጠም።
አቡ አል ሀሰን አሜሪካ በየካቲት ወር 2022 የቀድሞውን የአይ ኤስ መሪ አቡ ኢብራሂም አል ሀሽሚን በሶሪያ መግደሏን ካሳወቀች በኋላ ቡድኑን መምራት መጀመሩ ይነገራል።
ከስሙም ሆነ ከዜግነቱ ጋር በተያያዘ አወዛጋቢ የሆነው አቡ አል ሀሰን ሶስተኛው የተገደለ የአይ ኤስ መሪ ነው።
የቀድሞውን የቡድኑ መሪ አቡበከር አልባግዳዲ በ 2019 መግደሏን ያስታወቀችው አሜሪካ የአቡ አል ሀሰንን ግድያ ቀደም ብዬ አውቀዋለው ብላለች።
ግለሰቡ በደራኣ ግዛት ከሶሪያ ነፃ ሃይሎች ጋር በተደረገ ውጊያ በጥቅምት ወር አጋማሽ ህይወቱ ማለፉን ነው ቪኦኤ የአሜሪካ የመከላከያ ምንጮቹን ጠቅሶ ያስነበበው።
አሜሪካ በግድያው ተሳትፎ አለማድረጓ የተገለጸ ሲሆን ፥ እስካሁን ለግድያው ሃላፊነቱን የወሰደ የለም።
ዋይትሀውስ የመሪውን መገደል መልካም ዜና ነው ብሎታል።
የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል ጆን ኪርቢ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፥
የአይ ኤስ መሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተወገዱ መሆኑ ለፀረ ሽብር እንቅስቃሴው ሃይል ይጨምራል ነው ያሉት።
ከአቡ አል ሀሰን ግድያ ባሻገር ባለፉት ስምንት ወራት አምስት የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በአሜሪካ የአየር ድብደባ ተገድለዋል።
የከፍተኛ አመራሮቹ ግድያ የቡድኑን ታጣቂዎች በማመናመኑ አዳዲስ አባላትን ለመመልመል በማህበራዊ ሚዲያዎች ዘመቻ ላይ ይገኛል።
አይ ኤስ መሪዎቹ እየተገደሉ አሁንም በሶሪያና ኢራቅ የሽብር ጥቃት ቀጥሏል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ በመልዕክታቸው የአይ ኤስ ቀጣይ መሪ ማን እንደሚሆን የገለፁት የለም።