የአሜሪካ መንግስት ከትናንት በስትያ በአፍጋኒስታን ካቡል ጥቃጥ ባደረሰው ኤይኤስ ላይ ጥቃት አድርሻለሁ አለ
የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ ከትናንት በስቲያ በካቡል በርካቶችን በገደለው እና ባቆሰለው አይ ኤስ ላይ ኢላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት መሰንዘሩን አስታወቀ፡፡
በኮማንዱ ቃል አቀባይ ካፒቴን ቢል አርባን ስም የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው አሜሪካ አይኤስ ኬ ተብሎ በሚጠራው የአይ ኤስ ክንፍ ላይ የጸረ ሽብር ዘመቻ ጀምራለች፡፡ የአየር ላይ ጥቃቱ በሰው አልባ ድሮኖች የተከናወነ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ምልክቶች እንደሚገልጹት ከሆነ እስካሁን ኢላማውን የመታ ጥቃት ተፈጽሟል ነው የተባለው፡፡ በንጹሃን ላይ የደረሰ ጉዳም እንደሌለ ነው ማዕከላዊ ኮማንዱ ባወጣው መግለጫ ላይ ያሰፈረው፡፡
ከትናንት በስቲያ አይኤስ ኃላፊነቱን የወሰደበት ፍንዳታ በካቡል ሃሚድ ካርዛይ አውሮፕላን ማረፊያ መከሰቱ የሚታወስ ሲሆን በጥቃቱ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡ አሜሪካም በዚህ ጥቃት 13 ወታደሮቿን ማጣቷ ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ ኃላፊ ትናንት እንደገለጹት የሀገራቸው ኮማንደሮች አይኤስ ሌሎች ጥቃቶችን ሊያደርስ ይችላል በሚል ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን በተለይም የሮኬት፣ ወይም በተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ቦንድ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል እንደሚጠረጥሩ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በፍንዳታው ላይ የተሳተፉ ሃይሎችን እንደሚታደኑ ትናንትና ገልጸው ነበር፡፡ ታሊባን አፍጋንን መዲና ካቡል ከተቆጣጠረ እና የአፍጋን ፕሬዝዳንት ሀገር ከለቀቁ ሁለት ከሳምንታት ባለይ ሆኖታል፡፡