እስራኤል የቀረበባትን የዘር ማጥፋት ክስ ለመከላከል ዛሬ ፍርድ ቤት ትቀርባለች
ዘሄግ የሚገኘው የአለም ፍርድቤት (አይሲጄ) በደቡብ አፍሪካ የቀረበውን ክስ ለሁለት ቀናት ያደምጣል
እስራኤልና አሜሪካ ክሱን የተቃወሙ ሲሆን ብራዚልና ኮሎምቢያ ለደቡብ አፍሪካ ክስ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል
እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች በሚል በደቡብ አፍሪካ የቀረበባትን ክስ ለመከላከል ዛሬ ፍርድ ቤት ትቀርባለች።
በኔዘርላንድስ ዘሄግ የሚገኘው የአለም ፍርድ ቤት (አይሲጄ) ክሱን ለሁለት ቀናት ያደምጣል ተብሏል።
ደቡብ አፍሪካ በታህሳስ ወር እስራኤል የ1948ቱን የዘር ማጥፋት ወንጀል ኮንቬንሽን ተላልፋ በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሟን በመጥቀስ በአስቸኳይ በአለማቀፉ ፍርድ ቤት እንድትቀርብ ጥሪ ማድረጓ ይታወሳል።
የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ ኢይሎን ሌቪ ግን “የደቡብ አፍሪካ ግልጽ ያልሆነ ስም ማጥፋት ፖለቲካዊ ይዘት ያለውና ለሃማስ ሽፋን ለመስጠት ያለመ ነው” በሚል ተቃውመውታል።
አሜሪካም የደቡብ አፍሪካን የዘር ማጥፋት ክስ ውድቅ ያደረገች ሲሆን፥ እስራኤል ፍልስጤማውያን ንጹሃንን ለመጠበቅ ይበልጥ ጥረት እንድታደርግ አሳስባለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማት ሚለር፥ “እስራኤልን የሚቃወሙ አካላት አይሁዳውያን እንዲጨፈጨፉ የሚፈቅዱ ናቸው፤ እስራኤል የሃማስን የሽብር ተግባራት ለማስቆም እርምጃ የመውሰድ መብት አላት” ሲሉ ተደምጠዋል።
ብራዚል እና ኮሎምቢያ በበኩላቸው በደቡብ አፍሪካ ለቀረበው የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ለፍልስጤማውያን ነጻ ሀገር የመሆን ትግል ስትደግፍ የቆየችው ደቡብ አፍሪካ፥ እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለውን እርምጃ በአፓርታይድ አገዛዝ ወቅት በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ከደረሰው በደል ጋር አመሳስላ ታቀርበዋለች።
የእስራኤል ባለስልጣናት የሚሰነዝሯቸው ሃሳቦችም ቴል አቪቭ በጋዛ ሃማስን ለመደምሰስ ሳይሆን ፍልስጤማውያንን ለማፈናቀልና ዜጎቿን ለማስፈር ያለመ ጦርነት መክፈቷን ያሳያል የሚሉ ትችት ስታቀርብ ቆይታለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው የፋይናንስ እና የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትሮቻቸው ያነሱትን “ፍልስጤማውያን ጋዛን በፈቃዳችሁ ልቀቁና እስራኤላውያን ይስፈሩበት” አስተያየት ተቃውመዋል።
እስራኤል በአለም ፍርድ ቤት በምትቀርብበት ዋዜማ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍም፥ “እስራኤል ጋዛን በቋሚነት መቆጣጠርም ሆነ ንጹሃንን ማፈናቀል አትፈልግም” ብለዋል።
ኔታንያሁ ሀገራቸው ንጹሃንን በመጠበቅና አለማቀፉን ህግ በማክበር ሃማስን ለመደምሰስ ውጊያ ላይ መሆኗን ቢጠቅሱም አሃዞች ግን ይህን አያረጋግጡም።
97ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ከ23 ሺህ 300 በላይ ንጹሃን ህይወታቸው ተቀጥፏል፤ ሚሊየኖች ከቀያቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
እስራኤል የጋዛ ሰርጥን በድጋሚ ልትቆጣጠር ትችላለች የሚለው ስጋታቸው ያየለው ዮርዳኖስ እና ግብጽ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መጠየቃቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።