እስራኤል በነዳጅ ጫኝ መርከቧ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አደረገች
ከኦማን ነዳጅ ጭና የተነሳችው መርከቧ በአረቢያን ባህር ላይ እያለች አደጋው እንደደረሰባት
በእስራኤል ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ በተፈጸመ በጥቃት የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል
እስራኤል በነዳጅ ጫኝ መርከቧ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ የኢራን እጅ እንዳለበት አስታወቀች።
በእስራኤል ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ሀሙስ ምሽት ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፤ በጥቃቱም የእንግሊዝ ዜግነት ያለውን የመርከቡን ካፒቴን ጨምሮ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል።
ከኦማን ባህረ ሰላጤ ነዳጅ ጭና የተነሳችው መርከቧ በአረቢያን ባህር ላይ እያለች አደጋው እንደደረሰባት ተነግሯል።
አደጋው የደረሰባት መርከብ ባለቤት የሆነው ማግኔት እያል፤ በመርከቡ ላይ ምን እንደተፈጠረ ለማጣራጥ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያኢር ላፒድ በትናትናው እለት በሰጡት መግለጫ፤ መርከቧ ላይ ለደረስው አደጋ ኢራንን ተጠያቂ በማድረግ “የኢራን የሽብር ተግባር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“ኢራን የእስራኤል ችግር ብቻ አይደለችም” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝም ሊል አይገባም ሲሉም ተናግረዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያኢር ላፒድ በጉዳዩ ላይ ከብሪታኒያው አቻቸው ዶሚኒክ ራብ ጋር እየተወያዩበት መሆኑን እና ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚወስዱት መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኢራን አረብኛ ቋንቋ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢራን በመርከቡ ላይ ጥቃት መፈጸሟን እና ጥቃቱም እስራኤል በሶሪያ ውስጥ በሚገኝ የኢራን አጋር የሆነ ድርጅት አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ መሆኑንም ገልጿል
የብሪታኒያ መንግስት ቃለ አቀባይ በበኩላቸው እውነታውን በፍጥነት ሊጣራ ይገባል ሲሉ አስታውቀዋል።
በመርከቧ ካፒቴን ላይ ለደረሰው ጉዳት ሀዘናቸውን በመግለጽም፤ በመርከቧ ላይ የደረሰው አደጋ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ምርመራ እንዲካሄድበትም ጠይቀዋል።