ፖለቲካ
አረብ ኤምሬትስ ለተጎዱ ፍልስጤማዊያን ድጋፍ ለማሰባሰብ ዘመቻ ጀመረች
ዘመቻው አረብ ኤምሬትስ ለፍልስጤም ህዝብ አፋጣኝ እርዳታ ለመስጠት የምታደርገው ጥረት አካል ነው
የእርዳታ ዘመቻው የፊታችን እሁድ በአቡ ዳቢ ይፋ ይሆናል
አረብ ኤምሬትስ በጋዛ ሰርጥ ጦርነት ለተጎዱ ፍልስጤማዊያን እርዳታ ለማቅረብ "ርህራሄ ለጋዛ" በሚል መሪ ቃል ዘመቻ ጀምራለች።
ዘመቻው ሰብዓዊ እርዳታን ለመሰብሰብ እና ማስተባበሪያ ማዕከላትን ለማቋቋም ወጥኗል።
በዘመቻው ረድኤት ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እና መገናኛ ብዙኸን እንደሚሳተፉ ተነግሯል።
ዘመቻው ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለፍልስጤም ህዝብ አፋጣኝ እርዳታ ለመስጠት የምታደርገው ጥረት አካል ነው።
የዘመቻው ዓላማ በጦርነቱ ለተጎዱ ፍልስጤማውያን አጋርነትን ለማሳየት፣ የሰብዓዊ ሁኔታዎችን ለማቃለል እና ክፉኛ ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ስቃይ ለማስታገስ ነው።
ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህጻናትን ጨምሮ የጋዛ ሰርጥ ህዝብ ከጤና አቅርቦቶች እና ከአጠቃላይ የንጽህና ቁሶች በመስተጓጎሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማቅረብ ታስቧል።
ዘመቻው የፊታችን እሁድ በአቡ ዳቢ ይፋ የሚሆን ሲሆን፤ የኤምሬትስ ቀይ ጨረቃ ባለስልጣን ቁጥጥር እንደሚያደርግም ተነግሯል።