የእስራኤል- ፍልስጤም ጦርነት ዓለም ኢኮኖሚ ምን ጉዳት ሊያደርስ ይችላል?
የጦርነቱ ጉዳት ለአስርት ዓመታት ሊዘልቅ እንደሚችል ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል
ክስተቱ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ለተጎዳው የዓለም ኢኮኖሚ ተጨማሪ ጫናዎችን ያደርሳል ተብሏል
የእስራኤል- ፍልስጤም ጦርነት ዓለም ኢኮኖሚ ምን ጉዳት ሊያደርስ ይችላል?
ለፍልስጤም ነጻነት እየተዋጋ መሆኑን የሚገልጸው ሀማስ ከስምንት ቀን በፊት በእስራኤል ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ጦርነት ተቀስቅሷል።
ይህ ጦርነት በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እየተጎዳ ባለው የዓለም አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርስ ተገልጿል።
የአሜሪካው ጂፒ ሞርጋን ባንክ ስራ አስኪያጅ ጄሚ ዲሞን በጉዳዩ ዙሪያ እንዳሉት የእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት የዓለምን ኢኮኖሚ ይጎዳል ብለዋል።
"ይህ ጦርነት በሀገራት መካከል በሚፈጠር ሽኩቻ ባንኮች ወለድ እንዲጨምሩ፣ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር፣ የኢንሹራንስ ወጪያቸው እንዲጨምር እና አለመተማመኖች እንዲያድጉ በማድረግ የንግድ ስራዎችን ይጎዳል" ሲሉ ተናግረዋል።
የእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት ተሳታፊዎች ቀስ በቀስ ሊጨምሩ ይችላሉ የሚል ስጋት እያየለ የመጣ ሲሆን ይህም የጂኦ ፖለቲካ ፍጥጫ፣ የምርት እንደልብ አለመዘዋወር፣ የዋጋ ንረት እና የዲፕሎማሲ ፍትጊያን ሊያመጣ ይችላልም ተብሏል።
የዓለም ነዳጅ እና ምግብ ዋጋ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት እንዲጨምር በማድረጉ በርካታ ሀገራት እና ኩባንያዎች ለተጨማሪ ጉዳቶች መዳረጉም ተገልጿል።
ይህ ሁሉ ችግር ባለበት የእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት መቀስቀሱ በጉዳት ላይ ላለው የዓለም ኢኮኖሚን ለበለጠ ጉዳት እንደሚዳርገውም በዘገባው ላይ ተገልጿል።
በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ የእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት በታዳጊ ሀገራት ላይ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ አለመረጋጋትን ያስከትላል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት የሰብዓዊ እርዳታ እጥረቱን የበለጠ ያወሳስባል ሲል አስጠንቅቋል።
በዓለም ላይ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጸው ተመድ አሁን ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ መከሰቱ እርዳታ ሲያገኙ የነበሩ ዜጎች እንዲቋረጥባቸው ሊያደርግም ይችላል ተብሏል።
እንደ ዘገባዎቹ ከሆነ በጦርነቱ ምክንያት በሚከሰት የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መናር ታዳጊ ሀገራት ወደከፋ ጫና እንዲገቡ ሊያደርግ ይችላልም ተብሏል።
በመሆኑም ጦርነቱ ቶሎ እንዲቆም ካልተዳረገ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር እየጨመረ እንዲሄድ ሊያደርግ ይችላል የተባለ ሲሆን ይህም ዓለማችንን ወደከፋ ጉዳት ሊያስገባት እንደሚችል ተሰግቷል።
አሜሪካ እና በርካታ ምዕራባዊያን ሀገራት ለእስራኤል ድጋፍ በማድረግ ላይ ሲሆኑ ዋሸንግተን የጦር መሳሪያ ሳይቀር ድጋፍ አድርጋለች።
ሀማስን ትረዳለች በሚል የምትጠረጠረው ኢራን በበኩሏ በንጹህ ፍልስጤማዊያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት ካልቆመ ወደ ጦርነቱ ልትገባ እንደምትችል አስጠንቅቃለች።