በደቡብ ምዕራባዊ እንግሊዝ ብሪስቶል ከተማ ቆሞ የነበረው የመታሰቢያ ሃውልቱ በሰልፈኞች ፈርሷል
በእንግሊዝ የብሪስቶል ከተማ ሰልፈኞች የባሪያ ፈንጋዩን ሃውልት ፈነገሉ
በጥቁሮች መብት የመከበር እንቅስቃሴ ከአሜሪካውያን ጎን በሞቆም ወደ አደባባይ የወጡ የእንግሊዝ ብሪስቶል ከተማ ሰልፈኞች በመታሰቢያነት የቆመውን የኢድዋርድ ኮልስቶንን ከነሃስ የተሰራ ሃውልት ፈንግለው ጥለዋል፡፡
ኢድዋርድ ኮልስቶን በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ባሪያ ነጋዴ ነው፡፡
ሃውልቱን በከተማዋ ጎዳናዎች በገመድ ሲጎትቱ የነበሩት ሰልፈኞቹ በከተማይቱ አቅራቢያ ወደሚገኘው የአቮን ወንዝ ወደብ ወስደው ወደ ወንዙ ስለመጣላቸውም ሲ.ኤን.ኤን ዘግቧል፡፡
ሁለት ቀናትን በዘለቀው ሰልፍ ከ10 ሺ የሚልቁ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ በሁለተኛው ቀንም ነው ሰልፈኞቹ ሃውልቱን ጎትተው የጣሉት እንደ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ፡፡
“ግለሰቡ ባሪያ ነጋዴ ነው፤ ለብሪስቶል ጥሩ ያደረገ ቢመስልም ያን ያደረገው ከአፍሪካ እያጓጓዘ ይሸጣቸው በነበሩ ሰዎች ጫንቃ ነው፤ ይህ ደግሞ ለከተማይቱ ነዋሪዎች ከስድብ በላይ ነው” ሲሉም ነው አንድ ጆን ማካሊስተር የተባሉ ሰልፈኛ በስፍራው ለነበሩ ለጋዜጠኞች የተናገሩት፡፡
የፈረሰው ሃውልት ባሪያ ንግድን ሊያስታውስ በሚችል ሌላ መታሰቢያ እንዲተካ ፊርማ የማሰባሰብ የኦን ላይን እንቅስቃሴዎች እንዳሉ የገለጸው ዘጋርዲያንም 11 ሺ ገደማ ሰዎች እንቅስቃሴውን ደግፈው ስለመፈረማቸው ዘግቧል፡፡
የተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ ህግ አውጪ የሆኑት ክሊቭ ሌዊስ የተባሉ ፖለቲከኛ ሃውልቱን መፍረስ ደግፈዋል፡፡
የብሪስቶል ከንቲባ ማርቪን ሪስም ቢሆኑ በተለሳለሰ ድምጸት ነው ስለሁኔታው የገለጹት እንደ ብዙሃን መገናኛዎች ዘገባ፡፡
በሃውልቱ ምክንያት የሃሳብ ልዩነቶች እንደነበሩ የገለጹም ሲሆን “የነበሩ ሰብዓዊ ውርደቶችን ለማስታወስ በሚል ስለመቆሙ የሚናገሩትን ማድመጥ ይገባል”ም ነው ያሉት፡፡
የሃገር ውስጥ ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፓቴል ግን ድርጊቱን አጣጥለዋል፡፡ ተቀባይነት የሌለው ሲሉም ነው የኮነኑት፡፡
የአካባቢው ፖሊስም በብዙዎች ጭብጨባና አድናቆት የታጀበውን ሃውልት የማፍረስ ድርጊት ፈጻሚዎች ለይቶ እንደሚጠይቅ እና ምርመራ እንደጀመረ አስታውቋል፡፡
“ባሪያ ፈንጋይ ነበር” የተባለው ኮልስቶን ማነው?
ኮልስቶን እ.ኤ.አ በ1636 በብሪስቶል እንደተወለደ የከተማይቱ ሙዚዬም የሰልፈኞቹን ቁጣ የቀላቀለ ድርጊት ተከትሎ ባወጣው ማብራሪያ ገልጿል፡፡
ግለሰቡ በብሪስቶል ይወለድ እንጂ አብዛኛውን ህይወቱን በዋና ከተማይቱ ለንደን ነው ያሳለፈው የሚለው ሙዚዬሙ “በባሪያ ፈንጋይነቱ ተጸጽቶ ንስሃ የገባ በጎ አድራጊ” እንደነበርም ያቀምጣል፡፡
በለንደን ይኖርና በንግድ ይተዳደር በነበረበት ጊዜ በምህጻረ ቃሉ “ራክ” (ሮያል አፍሪካን ካምፓኒ) በተሰኘ የወቅቱ የባሪያ ፈንጋይ ኩባንያ የ11 ዓመታት የአክሲዮን ባለድርሻ እንደነበር የሙዚዬሙ መግለጫ ይጠቁማል፡፡
ኩባንያው ከ1672 እስከ 1689 ባሉት 17 ዓመታት ከ100 ሺ በላይ ሰዎች ከምዕራብ አፍሪካ አጓጉዞ በካሪቢያንና በአሜሪካ ስለመሸጡ የኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል፡፡