የሁለቱ ኮሪያዎች የጋራ ጽህፈት ቤት ጋየ
ጽህፈት ቤቱ የጋየው ሃገራቱ በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ ጸረ ሰሜን ኮሪያ በራሪ ወረቀቶች መበተናቸውን ተከትሎ ፒዮንግያንግ በወሰደችው የበቀል እርምጃ ነው
ደቡብ ኮሪያ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ምክር ቤቷን ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርታለች
ፒዮንግያንግ የሁለቱን ኮሪያዎች የጋራ ጽህፈት ቤት አጋየች
ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የምትጋራውን የጋራ ጽህፈት ቤት አጋየች፡፡
ፒዮንግያንግ ካሶንግ በተባለች የድንበር ከተማዋ የሚገኘውን ባለ አራት ወለል ህንጻ ያጋየችው በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው መቃቃር እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ እንደሆነ የሴዑል ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ጸረ ፒዮንግያንግ መልዕክትን የያዙ በራሪ ወረቀቶች ሃገራቱ በሚወሰኑበት ድንበር አቅራቢያ መበተናቸውን ተከትሎ የተወሰደ የበቀል እርምጃ እንደሆነ የመሪው የኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ዮ ጆንግ ተናግረዋል ሲል ክዮዶ የተባለው የጃፓን ብዙሃን መገናኛ ዘግቧል፡፡
በራሪ ወረቀቶቹ ከድተው በደቡብ ኮሪያ በተጠለሉ የሰሜን ኮሪያ ዜጎች ነው የተበተኑት፡፡
ይህንኑ በማስመልከትም ኪም ዮ ጆንግ ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ ማስጠንቀቂያዎችን ሲሰጡ እና ሲዝቱ ነበር ተብሏል፡፡
ህንጻው ሙሉ በሙሉ መውደሙን የዘገቡ የደቡብ ኮሪያ መንግስት ብዙሃን መገናኛዎች ዜጎቹ ባጠፉት ጥፋት እንደሚጠየቁ ዘግበዋል፡፡
ሁኔታው ከወትሮው በተሻለ መልኩ እየተለሳለሰ የመጣው የሃገራቱ ግንኙነት ይበልጥ እንዳይሻክር እና ወታደራዊ መፋጠጦች እንዳይፈጠሩ አስግቷል፡፡
የፕሬዝዳንት ሙን ጃዔ ኢን ቢሮ የሃገሪቱን የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት አባላትን ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ በጉዳዩ ላይ አወያይቷል፡፡
ሆኖም በውይይቱ ፕሬዝዳንቱ አልታደሙም፡፡ ስለ ውይይቱ ሁኔታ የተሰጠ ዝርዝር መረጃም የለም፡፡
ጽህፈት ቤቱ እ.ኤ.አ በ2018 የፓንሙንጆን ስምምነት ተከትሎ ነበር የሃገራቱን ግንኙነት ለማስቀጠል በሚል የተቋቋመው፡፡ ልክ እንደ ኤምባሲ ሆኖ ያገለግልም ነበር፡፡