እስራኤል ከጋዛ ወታደሮቿን ለማስወጣት መስማማቷን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገለጹ
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አንቶኒ ብሊንከን አሜሪካ በጋዛ ያለው ጦርነት ከዚህ በላይ እንዲራዘም አትፈልግም ብለዋል
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ትላንት ከጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳቡን እንዲቀበሉ ግፊት አድርገዋል
እስራኤል ከጋዛ ወታደሮቿን ለማስወጣት ዝግጁ መሆኗን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ እስራኤል በጋዛ ለረጅም ጊዜ እንድትቆይ እና ጦርነቱ እንዲራዘም አሜሪካ እንደማትፈልግ ነው የገለጹት።
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ከሰሞኑ ለዘጠነኛ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ የዲፕሎማሲ ጉዞ ያደረጉት ብሊንከን፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም በባለፈው ሳምንት የተጀመረው የድርድር ሂደት መሳካት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ከእስራኤል ጋር በነበረን ንግግር ከተወሰኑ የጋዛ አካባቢዎች ወታደሮቿን ለማስወጣት ተስማምታለች ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ይህ ለድርድሩ ስኬታማነት በጎ ተጽእኖ የሚኖረው እንደሆነ ገልጸዋል።
በጋዛ እና በግብጽ መካከል ያለውን ፊላዴልፊያ የተባለውን ድንበር ቴልአቪቭ አሁንም የመልቀቅ ፍላጎት ባይኖራትም ከደቡባዊ ጋዛ ወታደሮቿን ልታስወጣ የምትችልበት እድል እንዳለ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ጋር በነበራቸው ውይይት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ነው ያሳወቁት።
ወታደሮቿን ከደቡባዊ ጋዛ ለማስወጣት የተስማማቸው እስራኤል ፊላዴልፊያ ከተባለው ግብጽ እና ጋዛን ከሚያዋስነው ድንበር ባለፈ ኔትዛሪም የተሰኝውን የሰሜን እና ደቡብ ፍልስጤምን የሚያገኛኝው ስፍራ እንደማትለቅ አስታውቃለች።
ሀገሪቱ ከነዚህ ስፍራዎች ወታደሮቼን አልስወጣም ያለችበት ምክንያት ደግሞ አካባቢው ሀማስ የጦር መሳርያ የሚያጓጉዝበት ነው በሚል ነው።
ሀማስ በበኩሉ የኔታንያሁ ጦር ከሙሉ ጋዛ ምድር ለቆ ካልወጣ የተኩስ አቁም ስምምነት አይታሰብም በሚል ባሳለፍነው እሁድ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆባይደን በትላንትናው እለት ከጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በተኩስ አቁም ድርደሩ ዙርያ በስልክ ተወያይተው ነበር።
በውይይታቸው ባይደን ይህን የድርድር ሀሳብ ወደ መቋጨት እና ወደ ትግብራ እንዲገባ ግፊት አድርገዋል።
በቅርቡ በካይሮ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር ላይ የሚኖሩ መስናክሎችን ማጥበብ እና ሀሳብን ለመቀበል ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ያሉት ባይደን ጦርነቱን ለማስቆም “የማቀራረቢያ ሀሳብ” በሚል የተሰየመው ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጨረሻ የተሻለው አማራጭ ነው ብለዋል።
10ኛ ወሩን ባስቆጠረው የጋዛ ጦርነት እስካሁን ከ40 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 92 ሺ ያህሉ ደግሞ የተለያየ ጉዳት አስተናግደዋል።