የእስራኤል ጦር የስድስት ታጋቾችን አስከሬን ከካን ዩኒስ ማስወጣቱን ገለጸ
የታጋቾች ቤተሰቦች የኔታንያሁ አስተዳደር ተኩስ በማቆም ወገኖቻቸውን እንዲያስለቅቅ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቷን ተናግረዋል
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ካን ዩኒስ ስድስት ታጋቾች ተገድለው መገኘታቸውን አስታወቀ።
ጦሩ ሟቾቹ ያጌዝ ቡችሽታብ፣ አሌክሳንደር ዳንሲይግ፣ አቭራሃም ሙንዱር፣ ዮራም ሜትዝገር፣ ናዴቭ ፖፕልዌል እና ቻይም ፔር መሆኗቸውን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
አስከሬናቸው ከካን ዩኒስ እንዲወጣ የገለጸው ጦሩ ለሟቾቹ ቤተሰቦች መርዶ መላኩን አብራርቷል።
በጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት ታግተው የተወሰዱ እስራኤላውያን ሞት መቀጠል በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ነቀፌታ እያስከተለባቸው ነው።
“ኔታንያሁ በታጋቾች እየቆመረ ነው” ያሉ የታጋቾች ቤተሰቦች በአደባባይ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ100 በላይ ታጋቾችን የሚያስለቅቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከመድረስ ይልቅ “ሃማስን መደምሰስ” ላይ አተኩረዋል በሚል ይወቀሳሉ።
የታጋቾች ቤተሰቦች በጋራ ያቋቋሙት ፎረምም በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ የኔታንያሁ አስተዳደር ከሃማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሞ ታጋቾች ይለቀቁ ዘንድ ጥሪ አቅርቧል።
“ቀሪዎቹ 109 ታጋቾች ሊለቀቁ የሚችሉት በድርድር ብቻ ነው፤ በመሆኑም አሁን ላይ ንግግር እየተደረገበት ያለው ረቂቅ በፍጥነት ተጠናቆ ስምምነት ላይ ሊደረስ ይገባል” ሲልም ነው ፎረሙ የጠየቀው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ለዚህ የታጋቾች ቤተሰቦች ፎረም ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም።
አሜሪካ በሀማስ እና እስራኤል መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ያቀረበችው ሃሳብ በቴል አቪቭ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ይፋ አድርጋለች።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በመካከለኛው ምስራቅ ዘጠነኛ ጉብኝታቸውን እያደረጉ የሚገኙት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከኔታንያሁ ጋር ዘለግ ያለ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው እስራኤል “በማቀራረቢያ ምክረሃሳቡ” ላይ መስማማቷን የተናገሩት።
አሜሪካ ባቀረበችው “የማቀራረቢያ ምክረሃሳብ” ዙሪያ የሃማስ ምላሽ እየተጠበቀ ነው።