እርምጃው የመጣው ረመዳን ከመግባቱ በፊት ሁኔታውን ለማረጋጋት በማሰብ ነው ተብሏል
እስራኤል የጀመረችውን የሰፈራ ፕሮግራም ለማቋረጥ ተስማማች።
እስራኤል ለበርካታ ወራት በዌስት ባንክ አዲስ የሰፈራ ውሳኔዎችን ከማድረግ ለመቆጠብ ተስማምታለች።
ሀገሪቱ ከአሜሪካ አስተዳደር ጋር በተደረገው የስምምነት ሰፈራዋን ለመግታት ስምም ላይ ደርሳለች።
በዚህም መሰረት የፍልስጤም አስተዳደር ሰፈራዎችን የሚቃወም ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ለጸጥታው ምክር ቤት ለማቅረብ የያዘውን ውጥን ለሌላ ጊዜ ያስተላልፋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ "እስራኤል ለአሜሪካ በመጪዎቹ ወራት ከጸደቁት ዘጠኝ አዳዲስ ሰፈራዎች ውጭ ሌላ ህጋዊ ሰፈራ እንደማታደርግ አሳውቃለች" ብሏል።
ነገር ግን “እስራኤል በዌስት ባንክ አካባቢ ህገ-ወጥ ህንጻዎችን ማፍረስን ለማቆም ቃል አልገባችም" በማለት አክሏል።
አል ዐይን ኒውስ ከምንጮቹ እንደሰማው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ለፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሀሙድ አባስ ሁለቱም ወገኖች የጀመሩትን እርምጃ ለስድስት ወራት እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የመረጡት ምንጮቹ፤ እስራኤል ለስድስት ወራት ያህል አዲስ የሰፈራ ውሳኔ ከማድረግ ወይም የፍልስጤም ቤቶችን ከማፍረስ ተቆጥባ በዌስት ባንክ ያለውን ሁኔታ ማረጋጋትና በአል-አቅሳ መስጊድ ደግሞ እንዳይባባስ ትሠራለች ብለዋል።
ፍልስጤም ደግሞ በጸጥታው ምክር ቤት ሰፈራን በመቃወም ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብን ለሌላ ጊዜ አስተላልፋለች ያሉት ምንጩ፤ በዌስት ባንክ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት ትሰራለች፤ በአሜሪካ እቅድ መሰረትም ከእስራኤል ጋር ቀስ በቀስ ወደ ቅንጅት ጸጥታ ትመለሳለች ብለዋል።
“የአሜሪካው ወገን በበኩሉ ሰፈራዎቹን በማውገዝ ከጸጥታው ምክር ቤት የወጣውን ፕሬዝዳንታዊ መግለጫ ለመደገፍ ቃል ገብቷል።"
የሁለቱን ሀገራት መፍትሄ በመያዝ፤ አሜሪካ ቆንስላዋን በኢየሩሳሌም እንድትከፍት ግፊት ያደርጋልም ሲሉ ተናግረዋል።
ፍልስጤማውያን በሰፈራው ላይ በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።
የአሜሪካ እርምጃ የመጣው ረመዳን ከመግባቱ በፊት ሁኔታውን ለማረጋጋት በማሰብ ነው ተብሏል።