“ፑቲን ዜለንስኪን እንደማይገድሉ ቃል ገብተውልኛል” - የእስራኤል የቀድሞ ጠ/ሚ
በፕሬዝዳንት ፑቲን ቃል መሰረትም ኬቭ የኔቶ አባልነት ጥያቄዋን ሰርዛለች ተብሏል
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን በንግግር ለማስቆም ጥረት ያደረጉት የእስራኤል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት በሞስኮ ከፑቲን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል
“ፑቲን ዜለንስኪን እንደማይገድሉ ቃል ገብተውልኛል” - የእስራኤል የቀድሞ ጠ/ሚ።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን አቻቸውን እንደማይገድሉ ቃል ገብተውልኛል አሉ የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት።
ቤኔት አንደኛ አመቱን ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚይዘውን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ ንግግር ለማስቆም ጥረት ካደረጉ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በመጋቢት ወር 2022 ወደ ሞስኮ በማቅናትም ከፑቲን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
በዚህ ምክክራቸውም ፑቲን የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የመግደል ፍላጎት እንዳላቸው ጠይቀዋቸው እንደነበር ከሰሞኑ በሰጡት ቃለመጠይቅ ተናግረዋል።
ከፕሬዝዳንት ፑቲን የተሰጣቸው ምላሽም “በፍጹም” የሚል እንደነበር ነው ያወሱት።
ከፑቲን የተገባላቸውን ቃል ለዜለንስኪ ወድለው ሲነግሯቸው፥ “እርግጠኛ ነህ አይገድለኝም?” ብለው እንደጠየቋቸውና “መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ” የሚል ማረጋገጫ እንደሰጧቸው ያብራራሉ።
ይህም ኬቭ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ለመቀላቀል የያዘችውን ውጥን እንድትሰርዝ ማድረጉን ነው እስራኤልን ለስድስት ወራት የመሩት ናፍታሊ ቤኔት ያስታወሱት።
ሞስኮም ዩክሬናውያን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ የማስፈታት እቅዷን እንድትሰርዝና ወደ ንግግር እንዲቀራረቡ እድል ፈጥሮ እንደነበርም በማከል።
ክሬምሊን ግን ለቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት አስተያየት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚይትሮ ኩሌባ ግን፥ “ፑቲን የሚታመን ሰው አይደለም” የሚል ምላሽን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
እስራኤል በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እጇን የማስገባት ፍላጎት እንደሌላት ብትገልጽም፥ ኢራን ለሩሲያ ድሮኖችን ማቅረቧን ተከትሎ ቴል አቪቭ ከኬቭ ወገን እንደምትሆን ይገመታል።
በሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት የፈጠረችው እስራኤል አሁንም ድረስ አሰላለፏን ከማሳወቅ ተቆጥባለች።