የእስራኤል በራሪዋ ተሽከርካሪ ሙከራ አደረገች
በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የሚፈጠር የትራንስፖርት ችግርን ትቀርፋለች የተባለችው በራሪ ተሽከርካሪ በ150 ሺህ ዶላር ለገበያ ትቀርባለች
በስአት 160 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም ያላት ተሽከርካሪ በ366 ሜትር ከፍታ ሰዎችን ታጓጉዛለች ተብሏል
በእስራኤል በራሪዋ ኤሌክትሮኒክስ ተሽከርካሪ ሙከራ ማድረጓ ተነግሯል።
ኤ አይ አር በተሰኘው የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰራችው አውሮፕላን ያለሰው ነው የበረራ ሙከራዋን ያደረገችው።
በስአት 160 ኪሎሜትር የመጓዝ አቅም ያላት ተሽከርካሪ በ366 ሜትር ከፍታ ትጓዛለች ተብሏል።
ሁለት ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላት አውሮፕላን (አንድ መንገደኛ እና የሚቆጣጠር ባለሙያ) አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጋ 160 ኪሎሜትሮችን መጓዝ ትችላለች።
የኩባንያው ስራ አስፈጻሚ ራኒ ፕላውት እንደሚሉት፥ በራሪ ተሽከርካሪዋ በቀጣይ በሰዎች ተሞክራ በ2024 ለገበያ ትውላለች።
ነገር ግን ሰዎች በዚህች አነስተኛ አውሮፕላን የመጓዝ እምነት እንዲኖራቸው የማድረግና የህግ ማዕቀፎችን የማዘጋጅት ስራ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ነው ያነሱት።
በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የሚፈጠር የትራንስፖርት ችግርን ትቀርፋለች የተባለችው በራሪ ተሽከርካሪ በ150 ሺህ ዶላር ለገበያ ትቀርባለች ነው የተባለው።
በድሮን ቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅ ስራን እየከወነች ያለችው ቴል አቪቭ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን እያበረታታች ትገኛለች።
በግል ኩባንያ የተሰራችውን አውሮፕላን በብዛት አምርቶ አጫጭር ጉዞዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብና በሽያጭ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘትም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆኗን ሬውተርስ አስነብቧል።