7ኛ ቀኑን በያዘው ግጭት የ170 ፍልስጤማውያንና 10 እሰራኤላውያን ህይወት አልፏል
እስራኤል የሀማስ መሪ ያህያ አል ሲንዋርን ቤት በአየር ኃይል ደብድባለች
የፀጥታው ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በእስራኤል ፍልስጤም በጉዳይ ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምታካሂደው የአየር ድብደባ እና ሀማስ ወደ እስራኤል የሚያስወነጭፋቸው ሮኬቶች ዛሬም ለሰባተኛ ቀን ቀጥለዋል።
እስራኤል በዛሬው ዕለት ጠዋት ላይ በጋዛ ሰርጥ በፈጸመችው የአየር ድብደባ የ26 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ በርካቶች መቁሰላቸው እና ሁለት ህንጸዎች መውደማቸው ተነግሯል።
በጋዛ የሚገኘው የሀማስ መሪ ያህያ አል ሲንዋር ቤትም የእሰራኤል የአየር ድብደባ ኢላማ እንደነበረ የቡድኑ ቴሌቪዥን መረጃ ያመለክታል።
በእስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ ነዋሪዎች ከሀማስ ከሚተኮስ ሮኬት ራሳቸውን በመከላከል ላይ ናቸው፡፡ ከሀማስ ሮኬት እየተወነጨፈ መሆኑን ተከትሎም በከተማዋ የማስጠንቀቅያ ድምጾች በስፋት እንደሚሰሙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ከሀማስ እየተተኮሱ ያሉ ሮኬቶችን ለመመከት ‘አይረን ዶም’ የተባለ የመከላከያ ስርአት ማስወንጨፉ ተሰምቷል።
የዛሬው ውጥረት የተከሰተው የእስራኤል ሚሳኤሎች ትናንት የስደተኛ መጠለያ ካሞፖችን በመምታት 8 ህጻናትን ጨምሮ የ10 ፍልስጤማውያን ህይወት ማለፉን ተከትሎ ነው።
የእሰራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በትናትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ በጋዛ እየተደረገ ያለው ዘመቻ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ይቀጥላል ብለዋል።
የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒያ በበኩላቸው ራሳችንን ከእስራኤል ለመከላከል የምንወስደው እርምጃ መቼም አይቆምም ነው ያሉት፡፡
በጋዛ ሰርጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት ሰባተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን በፍልስጤም በኩል እስካሁን 170 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፤ ከእነዚህም ውስጥ 41 ህጻናት መሆናቸው ነው የተነገረው።
ከ1 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ደግሞ መቁሰላቸውንም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።
በእስራኤል በኩል ደግሞ ግጭቱ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ እስካሁን 10 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ ሲሆን ፣ ከእነዚህም ውስጥ የ2 ሰዎች ሞት በትናትናው እለት የተመዘገበ ነው።
የበርካታ ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቅፍ ተቋማት የግጭቱ ሁኔታ እንዳሳሰበቻው እገለጹ ነው፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በጉዳዩ ላይ እንደሚመክርም ይጠበቃል። የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ዛሬ በጉዳዩ ላይ ይወያያሉ ተብሏል፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ውጥረቱን ለማርገብ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያፈላለግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ፣ ምክር ቤቱ እስካሁን ጉዳዩ ላይ እርምጃ ላለመውሰዱም አሜሪካን ተችተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከእሰራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር ፣ እስራኤል ከጋዛው ሀማስ እና ከሌሎች አሸባሪ ቡደኖች ከሚተኮሱባት ሮክቶች ረሷን ለመከላከል የምታደረገውን ጥረት አሜሪካ ትደግፋለች ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከፍልስጤሙ መሪ መሃሙድ አባስ ጋርም የተወያዩ ሲሆን ፣ በውይይታቸውም ኢየሩሳሌም ሁሉም እምነቶች በሰላም አብረው የሚኖሩባት እንድትሆን ባላቸው የጋራ ፍላጎት ላይ ተወያይተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ባይደን የአሜሪካ እና ፍልስጤም አጋርነትን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል፡፡