እስራኤል የወታደራዊ አገልግሎት ጊዜ እንዲራዘም ወሰነች
የእስራኤል መንግስት የጸጥታ ካቤኔ የአስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ጊዜን አሁን ካለው የ32 ወራት ወደ 36 ወራት ለማራዘም የቀረበውን እቅድ አጽድቆታል
የእስራኤል ጦር አዛዦች ተጨማሪ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው ሲገልጹ ቆይተዋል
እስራኤል የወታደራዊ አገልግሎት ጊዜ እንዲራዘም ወሰነች።
የእስራኤል መንግስት የጸጥታ ካቤኔ የአስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ጊዜን አሁን ካለው የ32 ወራት ወደ 36 ወራት ለማራዘም የቀረበውን እቅድ አጽድቆታል።
ካቢኔው በትናንትናው እለት ባደረገው ስብሰባ የ36 ወራቱ አስገዳጅ የአገልግሎት ጊዜ ለቀጣይ ስምንት አመታት ተግባራዊ እንደሚሆን ሮይተርስ የእስራኤሉን ዋይኔት ጠቅሶ ዘግቧል።
ይህ እቅድ በመጭው እሁድ ሁለም የካቢኔ አባላት በሚገኙበት ለምርጫ ሊቀርብ እንደሚችል ጠቅሷል።
የእስራኤል ጦር አዛዦች በጋዛ ከሀማስ ጋር የሚደረገውን ውጊያ እና ሊባኖስ ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው የሄዝቦላ ታጣቂ ጋር ያለውን ፍጥጫ ለመቋቋም ተጨማሪ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
እስራኤል ከዚህ በፊት ወታደራዊ አገልግሎት ያለመስጠት መብት የነበራቸው በሺዎቸ የሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ ተማሪዎች፣ ወታራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ረቂቅ ሰነድ አዘጋጅታለች።
የኦርቶዶክ ተማሪዎችን ለወታደርነት የመመልመል እቅዱ በአማኞቹ ተቃውሞ ገጥሞታል።ከዚህ በተጨማሪም እቅዱ "ተገቢ ነው" እና "ተገቢ አይደለም" የሚሉ ሁለት ሀሳቦች በእስራኤላውያን ዘንድ እንዲንጸባረቁ አድርጓል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ ያደረሰውን ከባድ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ለሀማስ አጋርነት ለማሳየት የሊባኖሱ ሄዝቦላ እና የየመኑ ሀውቲ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ጥቃት መክፈታቸው፣ እስራኤል የውጊያ ግንባሮቿን እንድታሰፋ እና የወታደር ቁጥር ለመጨመር እንድትንቀሳቀስ አስገድዷታል።