እስራኤል እና ሀማስ በመጀመሪያው ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት የመጨረሻውን የታጋቾች እና እስረኞች ለውውጥ ለማድረግ ተስማሙ
እስራኤል ባሳለፍነው ቅዳሜ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተኩስ አቁም የመጨረሻዎቹን በህይወት ያሉ ታጋቾችን ተቀብላለች

ሀማስ ታጋቾችን በሚለቅበት ጊዜ የሚያዘጋጃቸውን የመድረክ ትዕይንቶች የማያቆም ከሆነ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደማትለቅ እስራኤል ዝታለች
እስራኤል እና ሃማስ አራት የታጋቾች አስከሬንን በመቶዎች በሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስረኞች ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የተጀመረው እና በርካታ መሰናክሎችን የተጋፈጠው የጋዛው የተኩስ አቁም ስምምነት በተለያዩ ዙሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውን እስረኞች እና በሀማስ ስር የሚገኙ ታጋቾች እንዲለቀቁ ምክንያት ሆኗል፡፡
እስራኤል ከቅዳሜው የእስረኞች እና ተጋቾች ልውውጥ በኋላ ፍልስጤማውያን እስረኞችን የምትለቅበትን ጊዜ ማራዘሟን አስታውቃ ነበር፡፡
ቴልአቪቭ በዚህ ሳምንት እንደምትለቃቸው የሚጠበቁትን 23 ህጻናትን እና አንዲት ሴትን ጨምሮ 620 ፍልስጤማውያን እስረኞችን የመፈቻ ጊዜ ያዘገየችው “ታጋቾች በሚለቀቁበት ጊዜ ሀማስ የሚያዘጋጃቸው መድረኮች የዜጎቼን ክብር የሚነኩ ናቸው” በሚል ነበር፡፡
በቀጣይ ታጋቾች በሚለቀቁበት ጊዜም መሰል የመድረክ ላይ ፕሮግራሞች እንዳይኖሩ ይህ የማይሆን ከሆነ ስምምነቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል አስጠንቅቃለች፡፡
ባለፈው ወር በጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በህይወት የሚገኙ የመጨረሻ ዙር 6 ታጋቾች ቅዳሜ ዕለት በሁለት ህዝባዊ ስነ ስርዓቶች መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ሀማስ በበኩሉ እስራኤል በዚህ ሳምንት እንደምትለቃቸው የሚጠበቁትን ፍልስጤማውን እስረኞች ካልፈታች የሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ድርድር የማይታሰብ ነው ብሏል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በግብጽ አደራዳሪዎች በደረሱበት ስምምነት 620 እስረኞችን በአራት እስራኤላውያን ታጋቾች አስክሬን ዛሬ ምሽት ለመለዋወጥ ወስነዋል፡፡
ሀማስ በአሁኑ ወቅት 63 ታጋቾችን ይዞ የሚገኝ ሲሆን በእስራኤል መንግስት መረጃ መሰረት ከእነዚህ ውስጥ 32ቱ ህይወታቸው አልፏል ተብሎ ይታመናል፡፡
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተደረሰውን የ42 ቀናት የተኩስ አቁም ለማራዘም ስምምነት እስካልተደረገ ድረስ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ያበቃል።
ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን በዘላቂነት ለማቆም በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ውይይት እንዲጀምሩ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ውይይቶቹ ገና አልጀመሩም።