አሜሪካና ዩክሬን በውድ ማዕድናት ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ
ፕሬዝደንት ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በቀጣይ አርብ "ትልቅ ስምምነት" ለመፈረም ወደ ዋሽንግተን እንደሚመጡ ተናግረዋል

የፕሬዝደንት ትራምፕ ጦርነት በፍጥነት የማስቆም ፍላጎትና ለሞስኮ በጎ የሆነ አዝማማያ ማሳየት ዩክሬንንና ከአውሮፓውያንን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል
አሜሪካና ዩክሬን በውድ ማዕድናት ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።
አሜሪካና ዩክሬን በረቂቅ የውድ ማዕድናት ስምምነት ላይ መስማማታቸውንና ይህም ፕሬዝደንት ትራምፕ ጦርነቱን በፍጥነት ለማስቆም ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት ኪቭ የዋሽንግተንን ድጋፍ እንድታገኝ እንደሚያስችላት ተገልጿል።
ረቂቅ ስምምነቱ የአሜሪካን የደህንነት ዋስትና ወይም ቀጣይነት ያለው የመሳሪያ አቅርቦት ጉዳይን በግልጽ አለመጥቀሱንና ነገርግን አሜሪካ ዩክሬን "ነጻ፣ሉአላዊ፣ ደህንነቷ የተጠበቀ" እንዲሆን ትፈልጋለች" የሚል ይዘት ማካተቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዋሽንግተንና ኪቭ ወደፊት ሊኖር በሚችል የመሳሪያ አቅርቦት ጉዳይ እየተወያዩ መሆናቸውን ሮይተርስ ስምምነቱን በቅርብ የሚያውቅ አንድ ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በቀጣይ አርብ "ትልቅ ስምምነት" ለመፈረም ወደ ዋሽንግተን እንደሚመጡ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ይህ የሆነው ሁለቱ መሪዎች ኃይለቃል ከተቀያዩሩ በኋላ ነው።
ስምምነቱን አሜሪካ ለዩክሬን ላደረገችው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ እንደክፍያ የሚያዩት ፕሬዝደንት ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ስምሞነት ላይ ከተደረሰ በኋላ በዩክሬን የሰላም አስከባሪ ኃይል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ከሶስት አመታት በፊት በዩክሬን ላይ ዘመቻ የከፈተችው ሩሲያ ምንም የኔቶ ኃይል እንዲሰማራ አትፈልግም። የተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት ወደ ዩክሬን ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ በፍላጎታቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ባለፈው ሰኞ ሞስኮ ይህን እንደምትቀበል ቢገልጹም፣ ክሬሚሊን ማክሰኞ እለት አስተባብሏል።
የፕሬዝደንት ትራምፕ ጦርነት በፍጥነት የማስቆም ፍላጎትና ለሞስኮ በጎ የሆነ አዝማማያ ማሳየት ዩክሬንንና ከአውሮፓውያንን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ፕሬዝደንት ዘለንስኪን የማይወደድ "አምባገነን" ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን ዘለንስኪ ፕሬዝደንት ትራምፕ በተሳሳቱ መረጃዎች ተከበዋል የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።