እስራኤል በሽብር ክስ የተፈረደባቸው ሰዎች ቤተሰቦችን ከሀገሪቱ የሚያባርር ህግ አጸደቀች
አከራካሪው ህግ መንግስት የጥቃት አድራሾች ወላጆች፣ እህትና ወንድሞች እንዲሁም ልጆችን ከእስራኤል እንዲያስወጣ ይፈቅዳል
ህጉ በዋናነት ፍልስጤማውያን እና አረብ እስራኤላውያን ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል
የእስራኤል ፓርላማ መንግስት በሽብር ክስ የተፈረደባቸው ሰዎች ቤተሰቦችን ከሀገሪቱ እንዲያስወጣ የሚፈቅድ ህግ አጸደቀ።
አከራካሪው ህግ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ አባል ነው የቀረበው።
ህጉ የሽብር ተግባር በመፈጸም አልያም በማበራታታት ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው አካል ወላጆች፣ እህትና ወንድሞች እንዲሁም ልጆች ከሀገር ይባረራሉ ይላል።
እስራኤላውያንም ጭምር የዚህ ህግ ሰለባ መሆናቸው ቢገለጽም በዋናነት ፍልስጤማውያን እና አረብ እስራኤላውያን ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ተቃውሞ እየቀረበበት ነው።
የእስራኤል የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ህጉን ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ብለውታል።
አዲሱ ህግ አስቀድመው መረጃ ኖሯቸው ለፖሊስ ጥቆማ ያልሰጡ አልያም ለሽብር ጥቃቱ በተለያየ መልክ ድጋፍ የሰጡ ሰዎች የቤተሰብ አባላት ከእስራኤል እንዲወጡ ይደረጋል ይላል።
“ሽብርን ወይንም የሽብር ድርጅቶችን የሚያበረታቱ፣ የሚያደንቁ አልያም ሀዘናቸውን የሚገልጹ”ም ከሀገር እንደሚባረሩ አስቀምጧል።
በአዲሱ ህግ ከሀገር እንዲወጡ የሚደረጉትን ሰዎች ጉዳይ የሚያስፈጽመው የእስራኤል የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ነው።
እስራኤላውያንንም ጭምር ከሀገር ያስወጣል የተባለው ህግ በምክርቤት (ክኔሴት) ክርክር ሲደረግበት የተወሰኑ የምክርቤት አባላት ህጉ በአይሁድ እስራኤላውያን ዜጎች ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን መጠየቃቸውን ታይምስ ኦፍ እስራኤል አስነብቧል።
በምክርቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባሉ ሜራቭ ሚካኤሊ፥ “የይጋል አሚር ቤተሰቦች ወደየትም አይባረሩም” ሲሊ ተናግረዋል። ዪጋል አሚር የቀድሞውን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ዪሳቅ ራቢን የገደለ አክራሪ ይሁዲ ነው።
በወጣትነታቸው ግጭት በመቀስቀስና የሽብር ቡድኖችን በመደገፍ ጥፋተኛ ተብለው የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን ግቪር ቤተሰቦችስ በአዲሱ ህግ ከሀገር ይባረራሉ ወይ የሚል ጥያቄም ተነስቷል።
እስራኤላዊው የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ዳህሊያ ስቺንድሊን በበኩላቸው ህጉ በአረብ እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን ላይ ያነጣጠረ መሆኑ “ምንም ጥያቄ” የለውም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በዚህ ህግ አይሁዳውያን የእስራኤል ዜጎች ከሀገሪቱ ይባረራሉ ብዬ በፍጹም አልጠብቅም” ሲሉም ያክላሉ።
አይሁዳውያን በፍልስጤማውያን ላይ ለሚፈጽሙት ነውጠኛ ተግባር እስራኤል አንድም ጊዜ ሽብርተኛ የሚለው አገላለጽ ተጠቅማ እንደማታውቅም በመጥቀስ።
ከእስራኤል ህዝብ ውስጥ 20 በመቶው የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ፍልስጤማውያን ናቸው።
ከቴል አቪቭ በስተሰሜን ባለፈው ወር የጭነት ተሽከርካሪ አውቶብስ ገጭቶ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉና ከ30 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል። የጭነት ተሽከርካሪው ሾፌር እስራኤላዊ ዜግነት ያለው ፍልስጤማዊ መሆኑ መገለጹም አይዘነጋም።
በርካታ አረብ እስራኤላውያን ሃማስ ባለፈው አመት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲፈጽም በማህበራዊ ሚዲያዎች ለቡድኑ ድጋፋቸውን አሳይተዋል በሚል ተከሰው ጥፋተኛ ተብለዋል።
አዲሱ በሽብር ተግባር ተሳትፈው ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች ቤተሰቦችን ከእስራኤል ያስወጣል የተባለው ህግ አፈጻጸም ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉት።
ከእስራኤል የሚባረሩት ሰዎች ወደ ጋዛ ሊወሰዱ እንደሚችሉ ቢገመትም ከእስራኤል ወታደሮች ውጭ የእስራኤል ዜጎች በህጋዊ መንገድ ጋዛ እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም።