እስራኤል እና ሞሮኮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ተስማሙ
ሞሮኮ በትራምፕ አስተዳደር አደራዳሪነት ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ለማደስ የተስማማች 4ኛ ሀገር ናት
ሞሮኮ በትራምፕ አስተዳደር አደራዳሪነት ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ለማደስ የተስማማች 4ኛ ሀገር ናት
እስራኤል እና ሞሮኮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር መስማማታቸውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ አድርገዋል፡፡
በትራምፕ አስተዳደር አደራዳሪነት ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፣ ከባህሬን እና ከሱዳን በመቀጠል ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር በ2020 መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመጀመር የተስማማች አራተኛዋ የአረብ ሀገር ሆናለች፡፡
በትዊተር ገፃቸው "ዛሬ ሌላ ታሪካዊ ድል ተገኘ" ያሉት ትራምፕ "ሁለቱ ታላላቅ ወዳጆቻችን እስራኤል እና የሞሮኮ መንግሥት የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማድረግ ተስማምተዋል ይህም ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ትልቅ ድል ነው" ብለዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ሞሮኮ ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በመመስረት ከእስራኤል ጋር ይፋዊ ግንኙነቶችን ትጀምራለች ፣ ለእስራኤል የአየር ክልሏን የምትፈቅድም ሲሆን ሁሉም እስራኤላውያን ቀጥተኛ በረራዎችን እንዲያደርጉም ትፈቅዳለች፡፡
የኋይት ሀውስ ከፍተኛ አማካሪ ያሬድ ኩሽነር እንደተናገሩት ፣ ራባት እና ቴል አቪቭ ኤምባሲዎቻችን በፍጥነት ለመክፈት ዝግጅት ማድረግ ጀምረዋል፡፡
በእስራኤል እና በሞሮኮ ኩባንያዎች መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማስጀመርም ሁለቱ ሀገራት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ይህ ታሪካዊ ቀን እንደሚመጣ ሁል ጊዜም አምናለሁ ሁል ጊዜም እሰራ ነበር” ብለዋል ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ “ሰላምን ለማስፋት ፣ በእስራኤልን እና በመካከለኛው ምስራቅ ህዝቦች መካከል ሰላም ለማምጣት ላደረጉት ልዩ ጥረት” ፕሬዝዳንት ትራምፕን አመስግነዋል፡፡
የሞሮኮ ህዝብ እና የአይሁድ ህዝብ በዘመናት ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው በመጥቀስ ጠ/ሚ ኔታንያሁ በተጨማሪም ለሞሮኮው ንጉስ መሐመድ ስድስተኛ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም ለማምጣት ላደረጉት “ታሪካዊ ውሳኔ” ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡
"የሞሮኮ ነገሥታት እና የሞሮኮ ህዝብ በሀገራቸው ለሚገኙ የአይሁድ ማህበረሰብ ያሳዩትን ታላቅ ወዳጅነት ሁሉም እስራኤላዊ ያውቃል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ በእስራኤል እና ሞሮኮ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አድንቀዋል፡፡