እስራኤል የጦር መሳሪያ ወደ ዩክሬን እንደማትልክ አስታወቀች
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ጋንትዝ በዩክሬን ጦርነት "የኢራንን ተሳትፎ" እንዳለ ተናግረዋል
የእስራኤል፤ በዩክሬን ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ቢኖር የሰብአዊ ርዳታየማድረስ ፖሊሲ ነው ብላለች
እስራኤል የጦር መሳሪያ ወደ ዩክሬን እንደማትልክ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሩሲያ እስራኤል ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንዳትሰጥ በቅርቡ ማስጠቀቋን የሚታወስ ነው፡፡
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የሀገሪቱ የደህንነት ምክትል ሀላፊ ድሚትሪ ኔድሜዴቭ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ እስራኤል ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከሰጠች ከሞስኮ ጋር ለዘላለሙ ትቆራረጣለች ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
እናም እስራኤል በመከላከያ ሚኒሰትሯ ቤኒ ጋንትዝ በኩል ለክሬምሊን ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያ በሰጠችው ምላሽ ወደ ዩክሬን የምትልከው የጦር መሳሪያ እንደሌለ አረጋግጣለች፡፡
ጋንትዝ ለአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮች በሰጡት አጭር መግለጫ፤ “ ከዩክሬን ጋር የተያያዘ ፖሊሲያችን አይለወጥም - ከምዕራባውያን ጎን መቆማችንን እንቀጥላለን፣ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ግን አናደርግም” ብለዋል፡፡
እስራኤል በዩክሬን ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ቢኖር የሰብአዊ ርዳታ እና ህይወት አድን ማቴሪያሎች የማድረስ ፖሊሲ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ቀደም እንዳደረግነው ዩክሬንን በአቅማችን መደገፉን እንቀጥላለን ሲሉም አክለዋል፡፡
ጋንትዝ በዩክሬን ጦርነት አለ ስለሚባለው "የኢራንን ተሳትፎ" በተመለከተ ሲናገሩም ፤ ጉዳዩ በቅርበት እየተከታተልነው ነው ነገር ግን "ኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እየሰጠች እንደሆነ እና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ የላቁ የጦር መሳሪያዎችበን ልትሰጥ እንደምትችል አይተናል። ኢራናውያን ስልታዊ በሆነ መንገድ ቢዋሹም መሳሪያ በመሸጥ ላይ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አክለውም “እንዲህ ዓይነቱ የኢራን ጣልቃ ገብነት በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በሊባኖስ፣ በየመን እና በሌሎችም ቦታዎች ተፈጽሟል አሁንም እንደቀጠለ ነው” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን መሬት በመሬት የሚተኮሱ ሚሳይሎችን እና ተጨማሪ ድሮኖችን ለሩሲያ ለመስጠት መስማማቷን ሮይተርስ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ስምምነቱ የተደረሰው የኢራን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሞሀመድ ሞክቤር እና ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት መሳሪያው በሚቀርብበት ጉዳይ ለመወያየት በሞስኮ ጉብኝት ባደረጉበት በፈረንጆቹ ጥቅምት ስድስት ነው፡፡
ይህ የኢራን እርምጃ አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሊያበሳጭ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡