እስራኤል ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ከሰጠች ግንኙነቷን ሙሉ ለሙሉ እንደምታቆም ሞስኮ አስጠንቅቃለች
እስራኤል ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንዳትሰጥ ሩሲያ አስጠነቀቀች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ በሚል ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ካመራች ስምንት ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ይህ ጦርነት ሁለቱ ሀገራት በይፋ እየተዋጉ ቢሆንም ከጀርባ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው በዩክሬን ምድር ከ70 የዓለም ሀገራት ጋር እየተዋጋች መሆኗን ተናግረው ነበር።
ዩክሬን የሩሲያን ጦር ለመመከት ከበርካታ ሀገራት የጦር መሳሪያ ድጋፍ እየተደረገላት ሲሆን ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች እንዲሰጧት በመጠየቅ ላይ ትገኛለች።
እስራኤል ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንደምትሰጥ እየተገለጸ ሲሆን ሩሲያ በበኩሏ ለእስራኤል ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የሀገሪቱ የደህንነት ምክትል ሀላፊ ድሚትሪ ኔድሜዴቭ እንዳሉት እስራኤል ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከሰጠች ከሞስኮ ጋር ለዘላለሙ ትቆራረጣለች ብለዋል።
ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት እንደሌላት የምትጠቀሰው ኢራን ለሩሲያ የሰው አልባ የጦር መሳሪያዎች እየረዳች መሆኑን ዩክሬን ከዚህ በፊት መናገሯ ይታወሳል።
ኢራን በዩክሬን የቀረበባትን ክስ ብታስተባብልም በኬቭ ያሉ የቴህራን ዲፕሎማቶች ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውም ይታወሳል።
ኢራን በበኩሏ በዩክሬን ለተወሰደባት እርምጃ ተመሳሳይ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ መዛቷ አይዘነጋም።
ሩሲያ ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ የዩክሬን ከተሞችን በሚሳኤል እና ድሮን መደብደቧን ተከትሎ አሜሪካ እና የኔቶ አባል ሀገራት አዲስ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።
አሜሪካ ለዩክሬን ከ750 ሚሊዮን በላይ ዶላር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ድጋፍ እንደምታደርግ ከሰሞኑ ገልጻለች።