የአውስታሊያ በኢየሩሳሌም ጉዳይ እስራኤልን ያበሳጨ በተቃራኒው ፍልስጤማውያንን ያስደሰተ ውሳኔ አሳልፋለች
አውስትራሊያ ለምዕራብ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማነት ሰጥታው የነበረውን እውቅና ማንሳቷን በይፋ አስታውቃለች።
የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ በሰጡት መግለጫ ሀገራቸው እንደፈረንጆቹ በ2018 የሰጠችውንና "ምዕራብ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት" የሚለውን የቀድሞ አቋሟን ቀይራለች በለዋል።
ሚኒሰትሯ አክለውም "ጉዳዩ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል በሚደረገው የሰላም ድርድር ማዕቀፍ ውስጥ መፈታት አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
“የአውስትራሊያ ኤምባሲ ሁል ጊዜ በቴልአቪቭ ነበር እናም እዚያው ይቆያል” ነገር ግን የእየሩሳሌም ጉዳይ በዓለም አቀፍ ህጋዊ ውሳኔዎች ቀጥተኛ ድርድር ነው ቢፈታ የተሻለ ይሆናል ብለዋል ዋንግ።
አውስትራሊያ ውሳኔዋን ማሳወቋ ተከትሎ ፍልስጤማውያን ደሰተኛ መሆናቸው ቢገልጹም፤ በአስራኤል ባለስልጣናት በኩል ከፍተኛ ድንጋጤና ብስጭት መፍጠሩ እየተነገረ ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ የአውስትራሊያን ውሳኔ ውድቅ አድርገውታል።
አል-ዐይን ኒውስ የደረሰው መግለጫ እንደሚያመለክተው ላፒድ “የአውስትራሊያ ውሳኔ በመገናኛ ብዙሃን ለሚተላለፉ የውሸት ዜናዎች ፈጣን ምላሽ የመስጠት አይነት ነው፤ እናም የአውስትራሊያ መንግስት ሌሎች ጉዳዮችን በቁም ነገር እና በሙያዊ ሁኔታ እንደሚመራተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
“ኢየሩሳሌም የእስራኤል የዘላለም ዋና ከተማ ናት እናም ምንም ነገር አይለውጠውም” ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ካንቤራ ምዕራብ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርጋ የሰጠችውን እውቅና ማቋረጧን ይፋ ካደረገች ከጥቂት ሰአታት በኋላ በቴል አቪቭ የሚገኙትን የአውስትራሊያ አምባሳደርን ለማብራሪያ መጥራቱን።
በሌላ በኩል የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት የስራ አስፈታሚ ኮሚቴ ጸሃፊና የሲቪል ጉዳይ ሚኒስትር ሁሴን ሼክ የአውስትራሊያን ውሳኔ በደስታ ተቀብለውታል፡፡
"አውስትራሊያ የእየሩሳሌም ጉዳይ በዓለም አቀፍ ህጋዊነት መሰረት መፍትሄ እንዲጋኝ በሚል ላሳለፈችው ውሳኔ ትልቅ ክብር አለን" ሲሉም ነው ሁሴን አል ሼክ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት የተናገሩት።