በደቡብ አፍሪካ የተከሰሰችው እስራኤል በአለምአቀፉ ፍ/ቤት ልትቀርብ ነው
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ከሀማስ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች የሚል ክስ አቅርባለች
እስራኤል በደቡብ አፍሪካ የቀረበባትን ዋጋ የሌለው ክስ ለመከላከል ዘሄግ በሚገኘው አለምአቀፍ ፍርድ ቤት ትቀርባለች
በደቡብ አፍሪካ የተከሰሰችው እስራኤል በአለምአቀፉ ፍ/ቤት ልትቀርብ ነው።
እስራኤል በደቡብ አፍሪካ የቀረበባትን የዘርማጥፋት ክስ ለመከላከል ዘ ሄግ በሚገኘው አለምአቀፍ ፍርድ ቤት(አይሲጄ) እንደምትቀርብ የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ከሀማስ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች የሚል ክስ አቅርባለች።
እስራኤል የ1948ቱን የዘርማጥፋት ህግ አላከበረችም ስትል የከሰሰችው ደቡብ አፍሪካ፣ ፍርድ ቤቱ በአስቸኳይ እንዲያቀርባት ባለፈው አርብ ጠይቃ ነበር።
ቃል አቀባዩ ኢሎን ሊቪ እንደተናገሩት እስራኤል በደቡብ አፍሪካ የቀረበባትን ዋጋ የሌለው ክስ ለመከላከል ዘሄግ በሚገኘው አለምአቀፍ ፍርድ ቤት ትቀርባለች።
ሌቪይ "ለደቡብ አፍሪካ መሪዎች የምናረጋግጠው፣ ታሪክ ይፈርድባችኋል፤ ምህረትም አይኖረውም" ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ የፍልስጤምን ሀገር የመሆን ጥያቄ ለአስርት አመታት ደግፋለች።
ደቡብ አፍሪካ ፍልስጤማውያን የሚደርስባቸውን ጥቃት፣ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በአፖርታይድ ዘመን ከሚደርስባቸው ጭቆና ጋር ታመሳስለዋለች።
እስራኤል ይህን ንጽጽር አትቀበለውም።
የአለም ፍርድ ቤት ተብሎ የሚጠራው አይሲጄ በሁለት ሀገራት መካከል የሚፈጠር ግጭትን ይፈታል።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክሱን "መሰረተቢስ"ስትል አጣጥላዋለች።
ደቡብ አፍሪካን የወከሉት ጠበቆች በፈረንጆቹ ጥር 11 እና 12 የተቀጠረውን ችሎት ለመስማት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የደቡብ አፍሪካ አለምአቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ዲፖርትመንት በኤክስ ገጹ አስታውቋል።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት የተቀሰቀሰው፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ 240 እስራኤላውያንን በማገቱ እና 1200 የሚሆኑትን በመግደሉ ምክንያት ነው።
በጥቃቱ የተበሳጨችው እስራኤል ጋዛን በሚያስተዳድረው ሀማስ ላይ የከፈችው የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት እንደቀጠለ ነው።
እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደች ያለው እርምጃ በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ጦርነቱን የጀመረው ሀማስ ኃላፊነት መውሰድ አለበት የምትለው እስራኤል የንጹሃንን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰዷን ትገልጻለች።
ተኩስ እንዲቆም ጫና ቢደረግም፣ እስራኤል ፍቃደኛ አልሆነችም።