በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የተከሰሰችው እስራኤል “ክሱ መሰረተ ቢስ ነው” ብላለች
ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከሰሰች።
እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለውን እርምጃ በቀዳሚነት ከተቃወሙ ሀገራት አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ አሁን ደግሞ ወደ ተመድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ማቅናቷ ተነግሯል።
በዚህም “እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍሊስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው” ያለችው ደቡብ አፍሪካ፤ ሀገሪቱንም በበዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከሳለች።
ደቡብ አፍሪካ በትናትናው እለት ለፍርድ ቤቱ ባስገባችው ክስ እስራኤል በጋዛ የሃማስ ቡድን ላይ በወሰደችው እርምጃ በ1948 በወጣው የዘር ማጥፋት ስምምነት የተጣለባትን ግዴታ እየጣሰች መሆኗን ገለጻች።
በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍድር ቤት እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት እንድታቆም አስቸኳይ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቃለች።
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታቆም የሚያዝዝ ጊዜያዊ ወይም የአጭር ጊዜ እርምጃዎችን እንዲወስድም ፍርድ ቤቱን ጠይቃለች።
ይህም “በፍልስጤም ህዝብ ላይ የሚደርሰውን የበለጠ ከባድ እና ሊጠገን የማይችል ጉዳት ለመከላከል አስፈላጊ ነው” ብላለች።
በደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት የተከሰሰችው እስራኤል በበኩሏ “ክሱ መሰረተ ቢስ ነው” በማለት ምላሽ ሰጥታለች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለደቡብ አፍሪካ ክስ በሰጠው የመጀመሪያ ምላሽ የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጓል።
“በጋዛ ሰርጥ ፍልስጤማውያንን እንደ ከለላ በመጠቀም እና ሰብአዊ እርዳታን በመስረቅ ህዝቡን ለስቃይ እየዳረገ ያለውና ዋነኛው ተጠያቂው ሃማስ ነው” ብሏል የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።
እስራኤል ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት በኋላ በጋዛ እየፈጸመች ያለውን ድብደባም በጽኑ ከተቃወሙ ሀገራው ውስጥ ደቡብ አፍሪካ አንዷ ነች።
ደቡብ አፍሪካ፣ በሀማስ ላይ የአጸፋ እርምጃ እየወሰች ባለችው እስራኤል ላይ ተቃውሞዋን የገለጸችው ንጹሃን እየተጎዱ ነው በሚል ምክንያት ነው።
ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል የሚገኙ አምባሳደሯን መጥራቷ የሚታወስ ሲሆን፤ እስራኤልም ከደቡብ አፍሪካ ጠርታለች።
የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ መወሰኑም ይታወሳል።
እስራኤል ከጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት በኋላ በጋዛ እየፈጸመች ባለው ወታደራዊ እርምጃ የሞቱ ፍሊስጤውያን ቁጥር ከ21 ሺህ አልፏል።