እስራኤል የጋዛን ተኩስ አቁም ለስድስት ሳምንት አራዘመች
ሃማስ በአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ የቀረበውን የተኩስ አቁም ማራዘም ምክረሃሳብ እንደሚቀበል እስካሁን በይፋ አልገለጸም

በጥር ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ትናንት ሌሊት ተጠናቋል
የእስራኤል መንግስት የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነትን በስድስት ሳምንት ለማራዘም የቀረበውን ምክረ ሃሳብ አጸደቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በጥር ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ ትናንት ሌሊት ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ስምምነቱ ለ42 ቀናት መራዘሙን ያስታወቀው።
ኔታንያሁ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር ለአራት ስአታት ያህል በስልክ መወያየታቸው ተገልጿል።
ዊትኮፍ ያቀረቡት ምክረሃሳብ ስምምነቱ ለ42 ቀናት ሲራዘም በጋዛ ከሚገኙት ታጋቾች ግማሾቹ በመጀመሪያው የስምምነቱ መፈጸሚያ እለት ይለቀቃሉ ይላል።
ቀሪዎቹ ታጋቾች ደግሞ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ሲደረስ እንደሚለቀቁ ይጠቅሳል።
እስራኤል የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ ምክረሃሳብ ማጽደቋን የገለጸች ሲሆን የፍልስጤሙ ሃማስ ግን እስካሁን በይፋ አስተያየቱን አልሰጠም።
ሃማስ አስቀድሞ ሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ድርድር መጀመር አለበት እንጂ ተኩስ አቁሙን በ42 ቀናት ማራዘም ተቀባይነት የለውም ማለቱን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
በአሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር አደራዳሪነት በጥር 19 2025 የተደረሰው ስምምነት ሶስት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን፥ እስራኤል በሁለተኛው ምዕራፍ ከጋዛ ወታደሮቿን ሙሉ በሙሉ እንድታስወጣ የሚያስችል ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከመጠናቀቁ በፊት መደረስ እንዳለበት ያመላክታል።
ይሁን እንጂ ለ42 ቀናት የዘለቀውና በርካታ ታጋቾችና እስረኞች የተለቀቁበት የመጀመሪያ ምዕራፍ ከመጠናቀቁ በፊት በዶሃ ሊደረግ የነበረው ድርድር ሳይሳካ ቀርቷል። በካይሮ ከቀናት በፊት የተጀመረው ድርድርም ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ሃማስ የዊትኮፍን ምክረሃሳብ "እስካሁን አልተቀበለውም" ያለ ሲሆን፥ ቡድኑ አቋሙን ከለወጠ ግን እስራኤል ድርድር ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ጠቁሟል።
ሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ድርድር የማይሳካ ከሆነ እስራኤል ከ42 ቀናት በኋላ በጋዛ ዳግም ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ያቀረቡት ምክረሃሳብ ያሳያል።