የጋዛን ኢኮኖሚ ወደ ነበረበት ለመመለስና ለመልሶ ግንባታ 350 አመታት ሊወስድ ይችላል - ተመድ
የተመድ ኤጄንሲዎች ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ አውዳሚ ጦርነቶች ከተከሰቱባቸው ስፍራዎች መካከል ጋዛ እንዱ ነው ብለዋል
በጦርነቱ ከ227ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ 66 በመቶ የሚሆኑ መሰረተ ልማቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል
ጋዛን ከጥቅምት 7፣ 2023 በፊት ወደነበረችበት ለመመለስ 350 አመታትን ሊወስድ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ፡፡
የተመድ የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ጦርነቱ ነገ ካበቃ እና ጋዛን ወደ ቅድመ ጦርነት ደረጃዋ ለመመለስ 350 አመታት ሊወስድ እንደሚችል አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እጅግ ገዳይ እና አውዳሚ ወታደራዊ ዘመቻዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለትን የጋዛ ጦርነት ለመልሶ ግንባታ አስርተ አመታትን ሊወስድ እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ እንደሰነበቱ ይታወሳል፡፡
አሁን ጦርነቱ ከተጀመረ ከአንድ አመት በኋላ እየወጡ የሚገኙ አዳዲስ ሪፖርቶች ደግሞ የጋዛን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት መቶ አመታተን ሊወስድ እንደሚችል እያመላከቱ ነው፡፡
የመልሶ ግንባታው እና ኢኮኖሚውን ድጋሚ ለማነቃቃት የሚወስደውን ጊዜ ለማሳጠር እስራኤል የጣለችው የእንቅስቃሴ እገዳ ሊነሳ ይገባል ተብሏል፡፡
ከጦርነቱ በፊት ሀማስ በ2007 ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ጋዛ በእስራኤል እና በግብፅ ኢኮኖሚያዊ እገዳ ስር ነበር፡፡
በሃማስ እና በምዕራቡ ዓለም የሚደገፈው የፍልስጤም አስተዳደር በዌስት ባንክ መካከል የተደረጉ አራት ጦርነቶች እና መከፋፈል እንዲሁ በጋዛ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫናን አሳድረዋል፡፡
አሁን ያለው ጦርነት በግዛቱ ላይ አስከፊ ውድመት አስከትሏል፣ መንደሮች በሙሉ ወድመዋል፣ መንገዶች እና ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ፈርሰዋል።
መልሶ ግንባታው ከመጀመሩ በፊት በአስክሬን እና ባልፈነዱ ቦምቦች የተሞሉ ፍርስራሾች እና ተራሮች መጽዳት አለባቸው።
የተመድ የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከ2007-2022 በጋዛ የነበረው አመታዊ ጥቅል ምርት እድገት 0.4 በመቶ ሲሆን እስራኤል አሁን ተግባራዊ እያደረገች በምትገኝው እገዳ ጋዛን በ2022 ወደነበረበት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመመለስ 100 አመታትን ይፈልጋል ብሏል፡፡
እስራኤል እገዳው ያስፈለገው ሃማስ የጦር መሳሪያ እንዳያስገባ ለማድረግ ነው ስትል ታጣቂ ቡድኑን ለጋዛ ችግር ተጠያቂ አድርጋለች።
በተባበሩት መንግስታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ለሪፖርቱ ምላሽ ሲሰጡ "የጋዛ ህዝብ በሃማስ መያዙን እስከቀጠለ ድረስ የጋዛ ነዋሪዎች የወደፊት ተስፋ የላቸውም" ብለዋል።
በጥር ወር መጨረሻ የአለም ባንክ በጋዛ የደረሰው ጉዳት 18.5 ቢሊየን ዶላር እንደሚገመት አስቀምጦ ነበር፤ ይህ ግምት የእስራኤል ታንኮች እና የአየር ጥቃቶች በደቡባዊ ራፋህ እና በሌሎች ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው የጋዛ አካባቢዎች ጠንካራ ጥቃት መክፈት ከመጀመራቸው በፊት የተተነበየ ነበር፡፡
በሌላ በኩል መስከረም ላይ በሳተላይት ምስል ቀረጻ ተመስርቶ በተደረገ የተባበሩት መንግስታት ግምገማ በጋዛ ውስጥ ከሚገኙት ህንጻዎች ሩብ ያህሉ መውደማቸውን ወይም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስቀምጧል፡፡
ከ227ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ 66 በመቶ የሚሆኑ መሰረተ ልማቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግሯል።
በኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት የሚመራ አለም አቀፍ የእርዳታ ሰጭዎች ጥምር የሆነው ሼልተር ክላስተር የፈረሱትን ቤቶች ብቻ ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ሲያሰላ 40 ዓመታት እንደሚፈጅ አረጋግጧል።
እንደ ሳኡዲ አረብያ እና አረብ ኢምሬትስ ያሉ ሀገራት ለጋዛ መልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ቢሆኑም ጋዛ ከእስራኤል ቁጥጥር ነጻ ወጥታ ፍልስጤም ወደ ነጻ ሀገርነት የሚወስዳትን መንገድ ስትጀምር ብቻ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡