የጋዛን ተኩስ አቁም ለማራዘም በግብጽ ተደርጎ የነበረው ስብሰባ ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ
በምዕራባውን እና በአረብ ሀገራት መካከል በጋዛ ዕጣ ፈንታ ዙሪያ ሰፊ ልዩነት መፈጠር ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት እያወሳሰበ እንደሚገኝ ተነግሯል

ከግብጹ ድረድር በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጸጥታ ካቢኔያቸው ጋር አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል
ከአንድ ወር በላይ የዘለቀውን የጋዛውን የተኩስ አቁም የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ የተኩስ አቁሙን ለማራዘም በግብጽ ተደርጎ የነበረው ስብሰባ ያለስምምነት ተጠናቋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለድርድር ግብጽ ከሄደው ልዑካን ቡድን እና ከደህንነት ካቢኔያቸው ጋር በጉዳዩ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ካቢኔያቸው የግብጹን ድርድር እና የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም መጠናቀቅ ዙሪያ መምከሩ ከመገለጹ ባለፈ ዝርዝር የውሳኔ ሀሳቦች ይፋ አልተደረጉም፡፡
እስራኤል ለ42 ቀናት የተፈረመውን የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት የረመዳን ጾም እስከሚያልቅ ድረስ ለማራዘም ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን፤ ሀማስ በበኩሉ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቆ ዘላቂ ጦርነት ማቆም እና መልሶ ግንባታ የሚመከርበት ሁለተኛ ዙር ምዕራፍ ተኩስ አቁም እንዲጀመር ሞግቷል፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ ተኩስ አቁም በዛሬው ዕለት የሚጠናቀቅ መሆኑን ተከትሎ የግብጽ እና ኳታር አደራዳሪዎች አዲስ የተኩስ አቁም ምዕራፍ እንዲጀመር ለማግባባት በትላንትናው ዕለት ሙከራ አድርገዋል፡፡
ባለፈው ወር የተደረሰው ስምምነት 33 እስራኤላውያን ታጋቾችን እና አምስት የታይላንድ ዜጎችን ወደ 2000 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞች እንዲፈቱ እና ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ማስቆም ችሏል፡፡
የግብጽ እና ኳታር አሸማጋዮች ውሉን ለማጠናከር እና ዛሬ የሚያበቃውን የተኩስ አቁም ስምምነት ቅራኔዎች ለመፍታት ለሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት የተወሰነ ጊዜ ጠይቀዋል፡፡
ሆኖም እስራኤል እና ሃማስ በቁልፍ ጉዳዮች ላይ አሁንም የተራራቁ ሀሳባቸውን እያንጸባረቁ ከመቀጠላቸው ባለፈ አንድኛው ሌላኛውን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ፡፡
ይህም ተጨማሪ ታጋቾችን እና እስረኞችን መፍታት እንዲሁም ጦርነቱ ለዘለቄታው የሚቋጭ እርምጃዎችን ያካትታል የተባለው ሁለተኛው ምዕራፍ አተገባበገር ጥርጣሬ እንዲያጠላበት አድርጓል፡፡
በጋዛ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ በእስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን ወይም በምዕራባውያን እና በአረብ መንግስታት መካከል ምንም አይነት የስምምነት ምልክት የለም።
ይህ እርግጠኛ አለመሆን ደግሞ ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት የሚደረገውን የድርድር ጥረት እያወሳሰበ እንደሚገኝ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሃማስ እስራኤል በፍጥነት ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ድርድርእንድትገባ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያሳድር አርብ ዕለት ጠይቋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ያለ ስምምነት ቅዳሜ (ዛሬ) የሚጠናቀቅ ከሆነ ምን ሊከተል እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡
የእስራኤል ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም እስራኤል ቀሪ ታጋቶቿ ካልተመለሱ በጋዛ ጦርነቱን ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።