እስራኤል በራፋህ ጥቃት መጀመር የሚያስችላትን የውጊያ እቅድ አጸደቀች
በሃማስ የቀረበውን አዲስ የተኩስ አቁም እቅድ ውድቅ ያደረገችው ቴል አቪቭ ወደ ኳታር ተደራዳሪዎቿን እንደምትልክ አስታውቃለች
የአሜሪካ ባለስልጣናት “ንጹሃን ፍልስጤማውያንን መጠበቅ ያልቻለው ኔታንያሁ” ከስልጣን እንዲነሳ እየጠየቁ ነው
እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተማ ጥቃት መጀመር የሚያስችላትን የውጊያ እቅድ አጸደቀች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፥ በራፋህ ውጊያ ለመጀመር እና ሰላማዊ ሰዎችን ለማስወጣት የሚያስችለው እቅድ መጽደቁን አመላክቷል።
እስራኤል በራፋህ ጥቃት ለመክፈት ወታደራዊ ዝግጅት ብታደርግም ንጹሃንን ወደሌላ ስፍራ ለማዘዋወር ያደረገችውን ቅድመ ዝግጅት ግን አይጠቁምም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ቴል አቪቭ ከሶስት ቀናት በፊትም ከጋዛ ህዝብ ግማሹ ከሚገኝባት ራፋህ ሰላማዊ ሰዎችን ወደ “ሰብአዊ ደሴቶች” ለማዛወር ከአለማቀፉ ማህብረሰብ ጋር እየሰራሁ ነው ማለቷ ይታወሳል።
ንጹሃኑ የሚሰፍሩበት ቦታ ጊዜያዊ መጠለያና ምግብ የተሟላለት ይሆናል ከማለት ውጭ ግን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥባለች።
በራፋህ ንጹሃንን በማስወጣት በሃማስ ታጣቂዎች ላይ ዘመቻ መክፈቴ አይቀሬ ነው ያለው የኔታንያሁ አስተዳደር ከአጋራቸው አሜሪካ ጨምሮ አለማቀፍ ነቀፌታ እየገጠመው ነው።
የዋይትሃውስ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ “የእስራኤል የራፋህ ጥቃት እቅድን እስካሁን አልተመለከትንም፤ አይተን አስተያየት እንሰጥበታለን” ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከንም አሜሪካ እቅዱ ተፈጻሚ የሚሆንና ንጹሃንን የሚጠብቅ መሆኑን ማረጋገጥ አለባት ነው ያሉት።
በአሜሪካ ሴኔት አብላጫ መቀመጫ ያለው የዴሞክራት ፓርቲ መሪው ቹክ ሹመር፥ እስራኤላውያን የሀገራቸውን አለማቀፍ ክብር እያጎደፈ የሚገኘውን ኔታንያሁ እንዲተኩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ባይደንም የሹመርን ንግግር ያደነቁ ሲሆን በርካታ አሜሪካውያን የሚጋሩት ሃሳብ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
አሜሪካ ከረመዳን ጾም መግቢያ በፊት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረስ ተስፋ ብታደርግም እስራኤል ከሃማስ የሚቀርቡ የተኩስ አቁም ምክረሃሳቦችን ውድቅ ማድረጓን ቀጥላለች።
የፍልስጤሙ ቡድን በትናንትናው እለት 100 የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸውን ጨምሮ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እንዲፈቱና በምትኩ የእስራኤል ታጋቾችን ለመልቀቅ ያቀረበው አዲስ የተኩስ አቁም እቅድ ተቀባይነት አላገኘም።
የሃማስ እቅድ በፍጹም ተግባራዊ የሚሆን አይደለም ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት፥ ይሁን እንጂ እስራኤል ተደራዳሪዎቿን ወደ ኳታር እንደምትልክ ገልጿል።
ዋሽንግተን እና የአረብ ሀገራት አደራዳሪዎች እስራኤልና ሃማስ የራፋህ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጫና እያደረጉ ነው ተብሏል።