ኢራን በትናንትናው ዕለት ከ250 በላይ ሚሳኤል ወደ እስራኤል መተኮሷ ይታወሳል
የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን በእስራኤል ላይ የሮኬት ጥቃት ከፈተ፡፡
አንድ ዓመት ሊሆነው አምስተ ቀናት ብቻ የቀሩት የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን ኢራን እና እስራኤል ወደ መደበኛ ጦርነት እንዳይገቡ ተሰግቷል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሊባኖሱ ሂዝቦላህ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት የከፈተችው እስራኤል በትናንትናው ዕለት በኢራን ሚሳኤል ተመታለች፡፡
በኢራን እንደሚደገፉ የሚታመነው የየመኑ ሁቲ አማጺያን በእስራኤል ላይ የሮኬት ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ በሰጡት መግለጫ ቁድስ 5 በተሰኘው ሮኬት እስራኤልን አጥቅተናል ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኢራን የታጠቀቻቸው የሚሳይል ጦር መሳሪያዎች እና የእስራኤል የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂ ምን ይመስላል?
ቃል አቀባዩ አክለውም እስራኤል በጋዛ እና በሊባኖስ የጀመረችውን ጥቃት ካላቆመች በእስራኤል ላይ ጥቃታችን እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡
እስራኤል በሁቲ አማጺያን ስለደረሰባት ጥቃት እስካሁን ያላሳወቀች ሲሆን በኢራን እና አጋሮቿ ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኢራን ስህተት ሰርታለች ያሉ ሲሆን ለዚህ ስራዋ ደግሞ ዋጋ ትከፍላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
አሜሪካ የኢራንን ጥቃት አውግዛ በቀጣይ ከእስራኤል ጋር የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ የዛተች ሲሆን የኢራን ነዳጅ ማውጫ ጣቢያዎች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ኢላማ ሊደረጉ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
የየመን አማጺያን ከሰሞኑ በቀይ ባህር በጉዞ ላይ ያለ መርከቦችን ያጠቁ ሲሆን መርከቦቹ ወደ እስራኤል ወደቦች በማምራት ላይ የነበሩ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት እየጨመረ ሲሆን መስከርም ወር ላይ ዋጋው ቀንሶ የነበረው ዓለም ነዳጅ ዋጋ ዳግም በማሻቀብ ላይ ይገኛል፡፡