የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የሰብአዊ እርዳታ ስርጭቱን እያስተጓጎለ ነው- ተመድ
የተመድ የጸጥታው ምክርቤት ወደ ጋዛ እርዳታ እንዲገባ የሚያሰችለውን በአረብ ኢምሬትስ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በትናንትናው እለት አጽድቋል።
ሩሲያ የውሳኔ ሀሳቡ ግጭት እንዲቆም የሚያስችል ማሻሻያ አንቀጽ እንዲካተትበት ብትጠይቅም፣ በአሜሪካ ተቃውሞ ምክንያት ሳይካተት ቀርቷል
ተመድ የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የሰብአዊ እርዳታ ስርጭቱን እያስተጓጎለ ነው አለ።
የተመድ የጸጥታው ምክርቤት ወደ ጋዛ እርዳታ እንዲገባ የሚያሰችለውን በአረብ ኢምሬትስ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በትናንትናው እለት አጽድቋል።
ነገርግን የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እስራኤል እያካሄደችው ያለው ወታደራዊ ዘመቻ በእርዳታ ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፍጠሩን ገልጿል።
ሩሲያ የውሳኔ ሀሳቡ ግጭት እንዲቆም የሚያስችል ማሻሻያ አንቀጽ እንዲካተትበት ብትጠይቅም፣ በአሜሪካ ተቃውሞ ምክንያት ሳይካተት ቀርቷል።
ሩሲያ ግጭት የማይቆም ከሆነ እርዳታ ማድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን በመግለጽ ነበር 13 ሀገራት የውሳኔ ሀሳቡን ሲደግፉት ድምጸ ተአቅቦ ያደረገችው።
ሀማስ በጋዛ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት የተመድ የውሳኔ ሀሳብ በቂ አይደለም ብሏል
ሀማስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እየዛቱ ያሉት አሜሪካ እና እስራኤል ሀማሰ እንደገና ተደራጅቶ ጥቃት እንዲፈጽም ያስችለዋል በማለት የተኩስ አቁም ሀሳብን አይቀበሉትም።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እስራኤል በምድር እና በአየር እያደረሰች ባለው ጥቃት እየጨመረ ያለው የሰው ጉዳት እና የሰብአዊ ቀውስ እያሳሰባቸው መሆኑን እየገለጹ ነው።
ተመድ አሁን ያለው የእርዳታ አቅርቦት ከሚፈለገው 10 በመቶ ያህል ነው ብሏል።
እስራኤል ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ 5405 ምግብ፣ ውሃ እና የመድሃኒት አቅርቦት የጫኑ መኪኖች መግባታቸውን ገልጻለች።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው በጦርነቱ 20057 ሰዎች ሲገደሉ 53320 የሚሆኑት ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።
እስራኤል በጋዛ በእግረኛ ወታደር ጥቃት ከጀመረችበት ጥቅምት መጨረሻ ሳምንት ወዲህ 140 ወታደሮች እንደተገደሉባት ማስታወቋ ይታወሳል።