እስራኤል እና ሃማስ በግብጽ እየተካሄደ በሚገኘው ድርድር ምን አሉ?
ሃማስ እስራኤል በጋዛ በዘላቂነት ተኩስ ካልቆመች ታጋቾችን ስለመልቀቅ አልደራደርም ብሏል
እስራኤል በበኩሏ የሰብአዊ ተኩስ አቁም እንጂ በዘላቂነት ተኩስ ለማቆም እንደማትፈልግ ገልጻለች
አሜሪካ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም በግብጽ “ወሳኝ” ድርድር እየተካሄደ መሆኑን አስታወቀች።
ይሁን እንጂ ሃማስ እና እስራኤል እያቀረቡት የሚገኙት ቅድመሁኔታ የካይሮውን ድርድር ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
የሃማስ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ ትናንት ካይሮ ከገቡ በኋላ የተጀመረው ድርድር በጋዛ ተኩስ ስለሚቆምበትና ታጋቾች ስለሚለቀቁበት ሂደት በስፋት እንደተመከረበት ሬውተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
በጋዛ ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ የእስራኤል ታጋቾችን የያዘው የፍልስጤሙ ኢስላሚክ ጂሃድ ቡድን መሪዎችም በቀጣይ ቀናት ወደ ግብጽ እንደሚያመሩ ነው የተነገረው።
የዋይትሃውስ ቃል አቀባዩ ጆን ኪርቢ በካይሮ እየተካሄደ በሚገኘው ድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ተናግረዋል።
የሃማስ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ የሚዲያ አማካሪው ታሄር አል ኖኖ ግን እስራኤል በጋዛ ወረራዋን ካላቆመች ሃማስ የእስራኤል ታጋቾችን የመልቀቅ ድርድር ውስጥ መግባት አይፈልግም ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ሃማስ በዘላቂነት ተኩስ ቆሞ ለፍልስጤማውያን በፍጥነት የሰብአዊ ድጋፍ ማድረስ ሲጀመር የታጋቾቹ ጉዳይ ወደ ጠረጼዛ ይምጣ የሚል አቋም መያዙንም ነው ያነሱት።
"እስራኤል ወረራዋን በቀጠለችበት ሁኔታ ስለድርድር ማውራት አንችልም፤ ታጋቾችን ስለማስለቀቅ ለመነጋገር መጀመሪያ ወረራው ይቁም” የሚል ሃሳባቸውንም አጋርተዋል።
ሃማስ በካይሮው ድርድር ለሰብአዊ ድጋፍ ሲባል ጦርነቱ ጋብ ይበል የሚለውን የእስራኤል ሃሳብ እንደማይቀበለው ገልጿል፤ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚደረስ ካልሆነ ንግግራችን ጉንጭ አልፋ ነው የሚል አቋም መያዙንም ነው የቡድኑ መሪ የሚዲያ አማካሪ የተናገሩት።
በግብጽ ስለሚደረገው ድርድር በይፋ መግለጫ ያላወጣችው ቴል አቪቭ ከዚህ ቀደም ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረስ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት በሰጡት መግለጫም “ሃማስ የእስራኤል ስጋት እንዳይሆን አድርገን እስካልደመሰስነው ድረስ በጋዛ ጦርነቱ አይቆምም” ብለዋል።
እስራኤል በፍልስጤማውያን ንጹሃን ላይ እያደረሰችው ያለው በደል አሳሳቢነትን መግለጽ የጀመረችው አሜሪካ፥ ቴል አቪቭ የምትወስደው እርምጃ በሃማስ ታጣቂዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዲሆን ጠይቃለች።
ሁለተኛው የእስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርብ ጊዜ ይፈረማል ብለው እንደማይጠብቁ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም የታጋች እና እስረኛ ልውውጥ ስምምነት እንዲደረስ “ግፊት እያደረግን ነው” ብለዋል።
አሜሪካ በጋዛ ዘላቂ ተኩስ እንዲቆም የሚቀርቡ ጥሪዎችን ከእስራኤል ጎን በመቆም ስትቃወም የቆየች ሲሆን፥ የካይሮው ድርድርም በዘላቂነት ተኩስ የሚቆምበት እንዲሆን ፍላጎቷን አላሳየችም።