እስራኤል የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲን አገደች
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “በሽብር ተግባር የተሳተፉ የኤጀንሲው ሰራተኞች ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ብለዋል
እስራኤል የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ሰራተኞች በጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት ተሳትፈዋል በሚል ስትከስ ቆይታለች
የእስራኤል ፓርላማ የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ በሀገሪቱ ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ ውሳኔ አሳለፈ።
ውሳኔው የእስራኤል አጋር የሆኑ ምዕራባውያን ሀገራት የጋዛ ሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ ነው በሚል የሚያቀርቡትን ስጋት ይበልጥ የሚያጠናክር ሆኗል።
እስራኤል ግን የተወሰኑ የየፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ ሰራተኞች በጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት ተሳትፈዋል፤ አንዳንዶቹም የሃማስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች አባላት ናቸው በሚል ስትወቅስ ቆይታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም “በእስራኤል ላይ በተፈጸሙ የሽብር ተግባራት ላይ የተሳተፉ የኤጀንሲው ሰራተኞች ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ማለታቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ሃላፊው ፊሊፕ ላዛሪኒ በበኩላቸው የእስራኤል ፓርላማ ያሳለፈው ውሳኔ የመንግስታቱ ድርጅት መመስረቻ ቻርተርንም ሆነ የአለማቀፉን ህግ የጣሰ መሆኑን ገልጸዋል።
“ውሳኔው በአዲስ መልክ የተጀመረ የድርጅቱን ስም የማጥፋት ዘመቻ እና ለፍልስጤማውያን ስብአዊ ድጋፍ የማድረስ ድርሻውን ህጋዊ ማዕቀፍ የማሳጣት አካል ነው” ሲሉም በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የእስራኤል ፓርላማ ትናንት ያሳለፈው ውሳኔ አሜሪካን ጨምሮ የቴል አቪቭ አጋሮች ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡትን ወቀሳ ይበልጥ የሚያባብስ ነው ተብሏል።
እስራኤል ባለፉት ሶስት ሳምንታት በሰሜናዊ ጋዛ ዳግም የጀመረችው የተጠናከረ ዘመቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ለዳግም መፈናቀል ዳርጓል።
የፍልስጤም የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ከ100 ሺህ በላይ ንጹሃን በጃባሊያ፣ ቤት ላሂያ እና ቤት ሃኑን ከምግብና ህክምና ድጋፍ ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል ብሏል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በጃባሊያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ወረራ በመፈጸም ከ100 በላይ ታጣቂዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።
ሃማስም ሆነ የሆስፒታሉ አመራሮች ግን በሆስፒታሉ ውስጥ ታጣቂዎች አልነበሩም በሚል ክሱን ውድቅ አድርገዋል።
እስራኤል ሃማስ በድጋሚ እንዳይደራጅ ለማድረግ በሚል የጀመረችው ጥቃት እና የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲን በህግ ማገዷ ለአንድ አመት በከባድ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ የከረሙትን ፍልስጤማውያን ሰቆቃ ያበዛዋል ተብሏል።