የሀማስ መሪ ግድያን ኔታንያሁ የጋዛውን ጦርነት ለመቋጨት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የቀድሞ የእስራኤል ጀነራል ተናገሩ
የኔታንያሁ አስተዳደር ታጋቾችን ማስመለስ እና ወደ ድንበር አካባቢ ተመልሶ ደህንነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ተብሏል
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከጋዛ ለመውጣት ግልጽ ስትራቴጂ የላቸውም በሚል እየተተቹ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛውን ጦርነት ለማቆም የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ሞት የፈጠረውን እድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የቀድሞ የእስራኤል ጄነራል ተናግረዋል፡፡
ጡረታ የወጡት የእስራኤል ጄኔራል ጂዮራ ኢላንድ የኔታንያሁ አስተዳደር ይህን አጋጣሚ ታጋቾችን ለማስመለስ እና ጦርነቱን ለማስቆም የማይጠቀሙበት ከሆነ እስራኤል ለአመታት የተራዘመ ጦርነት ውስጥ እንደምትዘልቅ አስጠንቅቀዋል፡፡
ከሲንዋር ግድያ በኋላ የኔታንያሁን ከጋዛ የመውጫ ስትራቴጂ ከሚጠይቁ እና ከሚተቹ የቀድሞ የመከላከያ አመራሮች መካከል ኢላንድ አንዱ ናቸው፡፡
ከሀማስ ታጣቂዎች ነጻ ለማድረግ ቢያንስ ሁለት ዙር ዘመቻ ተግባራዊ ከተደረገባቸው ሰሜናዊ ጋዛን በመሳሰሉ ቦታዎች ባለፉት 3 ሳምንታት ለሶስተኛ ጊዜ እስራኤል ድጋሚ ጦሯን ልካለች፡፡
የእስራኤል ጦር ፈጣን ወሳኝ እርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ ሰራዊቱ ቋሚ ወታደራዊ ስምሪትን የሚፈልግ ክፍት ዘመቻ ውስጥ ራሱን እየከተተ ይገኛል ሲሉ የቀድሞ ወታደራዊ አዛዦች ተችተዋል፡፡
“የእስራኤል መንግስት የእስራኤልን የፀጥታ ጽንሰ ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ የሚቃረን ድርጊት እያደረገ ነው” የሚሉት የቀድሞ ደቡባዊ እዝ አዛዥ ዮም-ቶቭ ሳሚያ በበኩላቸው፤ “ሀማስን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ስለማይቻል የኔታንያሁ አስተዳደር ታጋቾችን ስለማስመለስ እና ወደ ድንበር አካባቢ ተመልሶ ደህንነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ” አሳስበዋል፡፡
የተለያዩ ወታደራዊ ተንታኞች እስራኤል አሁን ላይ በሰሜናዊ ጋዛ በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ እያደረገች የምትገኝው ወታደራዊ ዘመቻ አካባቢውን ከሲቪሊያን በማጽዳት ከጦር ቀጠና ነጻ ዞን ለማቋቋም እና በስፍራው በዘላቂነት ለመቆየት አላማ ያለው ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ለዚህ ተደጋጋሚ ወቀሳ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ምላሽ ሲሰጡ እስራኤል ታጋቾችን ማስመለስ እንዲሁም የሃማስን ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም ከደመሰሰች በኋላ በጋዛ የመቆየት ፍላጎት የላትም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ቢሉም እስካሁን ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ ለቀው ስለሚወጡበት ግልጽ ስትራቴጂ አለማስቀመጣቸው በጋዛ ዙሪያ በያዙት አቋም ላይ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል፡፡
በቴልአቪቭ በሚገኘው የብሔራዊ ደህንነት ጥናት ተቋም የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ኦፌር ሸላህ፤ ምንም አይነት መውጫ ስትራቴጂ ይፋ ባልተደረገበት የእስራኤል ጦር በጋዛ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ስጋት ተደቅኖበታል ብለዋል፡፡
የእስራኤል ጦር በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ሃማስ እንደያዘ የገመገመው 25 ሻለቃ ጦር ከረጅም ጊዜ በፊት ወድሟል፤ ግማሽ ያህሉ ሃይል ወይም ከ17 ሺህ-18ሺህ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
የእስራኤል ተደራዳሪዎች የተኩስ አቁም ስምምነት እና ታጋቾችን በማስለቀቅ ላይ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ድርድር ለመቀላቀል በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወደ ኳታር እንደሚበሩ የኔታኒያሁ ፅህፈት ቤት አስታውቋል ፤ነገር ግን የሐማስ አቋም ምን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን አልታወቀም፡፡