የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል በፈቃዳቸው ከሀላፊነት ለቀቁ
የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል ቤኒ ጋንትዝ በጋዛ እጣ ፈንታ ዙርያ ከኔታንያሁ አስተዳደር ጋር መስማማት አልቻሉም
ኔታንያሁ በጦርነቱ አጨራረስና በጋዛ ጉዳይ ስትራቴጂ ማቅረብ አለመቻላቸው በመንግስታቸው አጣማሪ ፓርቲዎች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል
የእስራኤል የቀድሞ መከላከያ ሚንስትር ቤኒ ጋንትዝ ከኔታንያሁ የጦር ካቢኔ አባልነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ጋንትዝ የጋዛውን ጦርነት መቀስቀስ ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ካቋቋሙት ሶስት አባላት ካሉት የጦር ካቢኔ ውስጥ አንዱ ሆነው ለ8 ወራት ዘልቀዋል።
ካቢኔው ጋንትዝን ጨምሮ የመከላከያ ሚንስትሩ ዮቭ ጋላንት እና ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁን በአባልነት የያዘ ሲሆን ጋንቴዝ ጦርነቱ በሚመራበት ሂደት ዙርያ ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል።
በቅርብ ጊዜያት በጦርነቱ የመጨረሻ ምዕራፍ አካሄድ እና በቀጣይ የጋዛ እጣ ፈንታ ዙርያ ከኔታንያሁ አስተዳደር ጋር መስማማት ያልቻሉት ጋንትዝ ልዩነታቸውን በይፋ ሲያንጸባርቁ ተስተውለዋል፡፡
የኔታንያሁ መንግስት እስከ ፈረንጆቹ ሰኔ 8 ድረስ በጋዛ ጉዳይ ሊከተል ያሰበውን ስትራቴጂ በግልጽ እንዲያሳውቃቸው ካልሆነ ከካበኔ አባልነታቸው እንደሚለቁ ያሳወቁት ጋንቴዝ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በካቢኔ አባልነታቸው እንደማይቀጥሉ አሳውቀዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው የቤኒ ጋንቴዝ ከሃላፊነት መልቀቅ የኔታንያሁን ጥምር መንግስት ላይ በቅጽበት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ባይኖርም የጠቅላይ ሚንስትሩን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዜጎችን ድጋፍ ሊያመናምነው ይችላል።
ጋንቴዝ ሲጠይቁ የነበሩትን ጦርነቱ የሚጠናቀቅበት ሁኔታ እና የጋዛ ቀጣይ እጣ ፈንታ ስትራቴጂ ጉዳይ የኔታንያሁ መንግስት ማቅረብ አለመቻሉ በመንግስታቸው አጣማሪ ፓርቲዎች ጨምሮ በሌሎች እስራኤላዊያን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
ይህ ደግሞ ፓርላማው እንዲበተን እና መንግስት ፈርሶ አዲስ ምርጫ እንዲደረግ ሲጠይቅ ለነበረው የጋንቴዝ ናሽናል ዩኒቲ ፓርቲ አለማ መሳካት መንገድ የሚጠርግ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።
ቤኒ ጋንቴዝ ትላንት በሰጡት መግለጫ ወታደሮቻችን በጋዛ እየተዋጉ ባሉበት ታጋቾችንም ሙሉ ለሙሉ ባለስለቀቅንበት ሁኔታ ኔታንያሁ ስትራቴጂያዊ ውሳኔ ለመወሰን ፖለቲካ ጋርዷቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ጥምር መንግስት 120 መቀመጫ ባለው ፓርላማ (ኬኔሴት) 64 መቀመጫዎች አሉት ሆኖም በጋዛ ጉዳይ ከቀድሞው የካቢኔ አባል ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ ያላቸው አጣማሪ ፓርቲዎቹ ለፓርላማው መበተን ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ እየተባለ ነው።
ሀማስ ሙሉ ለሙሉ ሳይደመሰስ ጦርነቱ መቆም የለበትም የሚል አቋም ያላቸው ፓርቲዎቹ እስራኤል ጋዛን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንዳለባት ከጋንቴዝ ሀሳብ ጋር ይስማማሉ።