ከኔታንያሁ አስተዳደር ጋር ጥምር መንግስት የመሰረቱ ፓርቲዎች የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ አስተዳደሩ እንዲፈርስ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል
የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል እና የኔታንያሁ ቀንደኛ ተቀናቃኝ ቤኒ ጋንዝ የእስራኤል ፓርላማ እንዲበተን እና ቅድመ ምርጫ እንዲደረግ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
በ6 የተለያየ ርዕዮት በሚከተሉ ፓርቲዎች ጥምረት የተመሰረተው የእስራኤል መንግስት ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን ከኔታንያሁ ሊክውድ ፓርቲ ከአጣማሪዎቹ ጋር የማይስማሙባቸው ጉዳዮች ጥቂት አልነበሩም፡፡
የሃማስን የጥቅምት 7 ጥቃት ተከትሎ 3 አባላት ያሉት የጦር ካቢኔ ያቋቋሙት ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ የናሽናል ዩንየን ፓርቲ መሪውን ጋንቴዝ የካቢኔው አባል አደርገዋቸዋል፡፡
የቀድሞው የጦር አዛዥ የነበሩት ጋንዝ እስራኤል በጋዛ እያደረገች ያለውን ጦርነት ከሚመሩ ቁልፍ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ጋንዝ ከጋዛ ጦርነት ጋር በተያያዘ አልተመለሱም ያሏቸውን 6 ነጥቦች የኔታንያሁ አስተዳደር ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ከካቢኔ ሀላፊነታቸው እንደሚለቁ ሲያስፈራሩ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡
የጦር መሪው ሊመለሱ ይገባል ብለው ካስቀመጧቸው 6 ነጥቦች መካከል ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በጋዛ ስለሚኖረው ሁኔታ እና በሀማስ እጅ ስለሚገኙ እስራኤላዊያን ታጋቾች ጉዳይ የሚመለከቱት ይገኙበታል፡፡
ኔታንያሁ እና ጋንዝ ጋዛን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እና በቀጣይ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት የላቸውም። በዚህ ጉዳይ ሶስተኛው የጦር ካቢኔ አባል ከሆኑት ከመከላከያ ሚንስትሩ ዮቭ ጋላንት ጋርም አይስማሙም፡፡
የመከላከያ ሚንሰትሩ ጋላንት እና ጋንዝ እስራኤል ሙሉ ለሙሉ ጋዛን ተቆጣጥራ ማስተዳደደር አለባት ሲሉ ኔታንያሁ በበኩላቸው ከዚህ በተቃራኒ ቆመዋል፡፡
የፓርላማው ይበተን የውሳኔ ሀሳብን ተከትሎ ምላሽ የሰጠው የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሊኩውድ ፓርቲ ሀገር ፈተና በሆነበት፣ ጥላት እየተወጋን ባለበት ወቅት የመንግስትን መበተን መጠየቅ የሃማስን እድሜ ማራዘም እና ታጋች እስራኤላዊያን በስቃይ እንዲቆዩ መፍቀድ ነው ሲል ተቃውሞውን ገልጿል፡፡
የኔታንያሁ አስተዳደር 120 መቀመጫዎች ባሉት ኬኔሴት (ፓርላማ) ጥምር መንግስት ከመሰረቱት ፓርቲዎች ጋር በጋራ 64 መቀመጫዎች ሲኖረው በአንጻሩ የጋንቴዝ ናሽናል ዩኒየን ፓርቲ 8 መቀመጫዎችን ይዟል፡፡
በቅርቡ የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች በዚህ ሁሉ ተቃውሞ ውስጥም እስራኤላዊያን ኔታንያሁ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው እንዲቀጥሉ የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ከበኔኒ ጋንዝ እና ከበኔንያሚን ኔታንያሁ ማን ጠቅላይ ሚንስትር ቢሆን ትመርጣላችሁ ተብለው ከተጠየቁት እስራኤላዊያን መካከል 36 በመቶዎች ኔታንያሁን ሲመርጡ 30 በመቶዎቹ ጋንዝን ብለዋል፡፡
ቀጣዩ የእስራኤል ምርጫ በ2026 ጥቅምት 26 የሚከናወን ሲሆን ጋንዝ ያቀረቡት የፓርላመው ይበትን ጥያቄ በኬኔሴቱ ተቀባይነት ካገኝ ኔታንያሁ የስልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ ወደ ምርጫ እንዲገቡ ይገደዳሉ፡፡